የአሜሪካ ሐኪሞች በፖሊዮ የተያዙ በርካታ ያልታወቁ ሰዎች አሉ ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ኒውዮርክ ግዛት የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናት በመቶዎች አሊያም በሺዎች የሚቆጠሩ ያልታወቁ በፖሊዮ የተያዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የጤና ባለሥልጣናቱ ይህንን ያሉት ባለፈው ወር በኒውዮርክ፣ ሮክላንድ ካውንቲ አንድ ያልተከተበ ግለሰብ በፖሊዮ ቫይረስ ምክንያት መንቀሳቀስ እንደተሳነው ከተገለጸ በኋላ ነው።
በግለሰቡ ላይ የተገኘው ቫይረስ በለንደን እና እየሩሳሌም ከተሞች ውስጥ በፍሳሽ ማስወገጃ ውስጥ ከተገኘው የፖሊዮ ቫይረስ ዝርያ ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል።
በዚህም ምክንያት ያደጉ የዓለም አገራት የክትባት ሥርጭታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
በሮክላንድ ካውንቲ የጤና ኮሚሽነር የሆኑት ዶክተር ፓትሪሺያ ሽናቤል፣ ባሉበት ግዛት የፖሊዮ ቫይረስ ሳይታወቅ እየተስፋፋ መሆኑ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
“መንቀሳቀስ የማይችል (ፓራላይዝ) የሆነ ሰው ካያችሁ በፖሊዮ የተያዘው አንድ ሰው ብቻ አይደለም። ይህ ክስተት ሥርጭቱ ከአንድ በመቶ ያነሰ ነው” ብለዋል ዶ/ር ፓትሪሺያ።
እንደ ዶ/ር ፓትሪሺያ ከሆነ በቫይረሱ የተያዘ ሰው በአብዛኛው ምልክት አይኖረውም አሊያም መጠነኛ ምልክቶች ይታዩበታል። እነዚህ የሚታዩት ምልክቶች ግን በአብዛኛው ይዘነጋሉ።
“በመሆኑም መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎችን ብንመለከት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምን አልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ክስተቶች አሉ” ብለዋል።
ዶክተር ፓትሪሺያ፣ ተመራማሪዎች በኒው ዮርክ ያለውን በፖሊዮ ቫይረስ ሳቢያ መንቀሳቀስ ያለመቻል ክስተትን በለንደን እና በእየሩሳሌም በቆሻሻ ውሃ ውስጥ ከተገኘው የፖሊዮ ቫይረስ ጋር ያለውን ግንኙነት ከሦስቱም ቦታዎች የዘረ መል ናሙናዎችን ከወሰዱ በኋላ እየመረመሩ መሆኑን ተናግረዋል።
“ይህ ለኒውዮርክ ብቻ ሳይሆን ለዓለማችንም በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ሁሉም ሕዝብ በትክክል ክትባት መውሰዱን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።
በክትባት ሳቢያ የሚከሰት ፖሊዮ
በቫይረሱ ሳቢያ መንቀሳቀስ የተሳነው አሜሪካዊው ግለሰብ የተያዘው በክትባት ሳቢያ በሚከሰተው ቫይረስ ነው።
ይህ የሚከሰተው አንዳንድ አገራት በክትባቶቻቸው ውስጥ ደካማ የሆነውን የቫይረስ ዓይነት በመጠቀማቸው ነው። አልፎ አልፎም ቫይረሱ ከሰውነት ጋር በመላመድ፣ በንጽሕና አጠባበቅ ጉድለት ሳቢያ ክትባት ወዳልወሰደ ሰው ይተላለፋል።
ዓለም አቀፍ ጉዞዎችም እነዚህ የበሽታ ክስተቶች ፖሊዮ መታየት ባልተለመደባቸው፤ ነገር ግን የክትባት ሥርጭታቸው ዝቅተኛ በሆነባቸው አገራት ሊዛመቱ ይችላሉ።
ምንም እንኳን ቫይረሱ ከዋናው ዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ደካማ ቢሆንም፣ በክትባት የሚመጣ ፖሊዮ ለጠና ህመም ሊዳርግ ይችላል።
ቫይረሱ በአከርካሪ አጥንት ላይ እንዲሁም በአንጎል ሥር የሚገኙ ነርቮች ላይ ጉዳት ያስከትላል።
በዚህም ሳቢያ በተለይ እግሮች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ያደርጋል። የመተንፈሻ ጡንቻ ከተጎዳም ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል።
አሜሪካ እና አብዛኞቹ ያደጉ አገራት ይህንን ለመከላከል በሕይወት ያለ ቫይረስ የሌለበትን አዲስ የክትባት ዘዴን እየተጠቀሙ ነው።
ዶክተር ሩፐርት እንደሚሉት በሕይወት ዘመናቸው በአሜሪካ በፖሊዮ የተያዘ ሰው አያለሁ ብለው አስበው አያውቁም።
በሮክላንድ ካውንቲ አንዳንድ አካባቢዎች በታሪክ ክትባት የወሰዱት 60 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ሲሆኑ ይህም ዝቅተኛ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ 2018ም የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር።
በእነዚህ አካባቢዎች በተለይ ሕጻናት የተሻለ ክትባት እንዲያገኙ ለማበረታታት የመስክ ባለሙያዎች ወደ ሥፍራዎቹ ተልከዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በቤክተን የፍሳሽ ማስወገድ ሥራ ወቅት በተወሰዱ ናሙና ላይ የፖሊዮ ቫይረስ ምልክቶች ከተገኙ በኋላ ተጨማሪ ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው።
የዩኬ የጤና ደኅንነት ኤጀንሲ የትኛው የለንደን አካባቢ በቫይረሱ ይበልጥ ተጎጂ እንደሆነ በቅርቡ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚሰጥ ይጠበቃል።












