የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ከፈረመች በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አሥመራ አቀኑ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለሥራ ጉብኝት የኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ገቡ።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ካለፈው ዓመት ግንቦት ወዲህ ወደ ኤርትራ በተደጋጋሚ በማቅናት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እና ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ የመግባባያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው እንደገለጹት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዛሬ ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም. ዕኩለ ቀን አሥመራ ገብተዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት መቀዛቀዙ የሚነገርላት ኤርትራ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነትን በተመለከተ በይፋ ያለችው ነገር ባይኖርም፤ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ተለያዩ አገራት እየተጓዙ ያሉትን የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ ተቀብላ እያስተናገደች ነው።
ሶማሊያ፤ ኤርትራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በወታደራዊ ሥልጠና ላይ የሚገኙ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ እነዚህን ሠልጣኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ ሲጥሩ እንደነበር ይታወቃል።
ከሰባት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ የአዲስ አበባ እና ሞጋዲሹ ግንኙነት ሻክሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት “የሶማሊያ መንግሥት እኛን ከማናገር ይልቅ በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል” በማለት ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው ላይ “እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል፤ ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ፣ እንድትፈራርስም፣ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግሥት አይደለንም፤ ቢሆን ኖሮ ልጆቹን ልኮ እዚያ አይሞትም” ብለው ነበር።
ከዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ንግግር በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በንግግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ አይደለችም ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም. በአገሪቱ ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ መንግሥታቸው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን ለማርገብ ፍላጎት ቢኖረውም፤ በአዲስ አበባ ያለው መንግሥት ግን ለውይይት ዝግጁ አይደለም ብለዋል።
ሰኞ ዕኩለ ቀን ላይ አሥመራ የገቡት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ የኤርትራ ማስታወቅያ ሚኒስትር በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ወደ ሶማሊያ የፕሬዝዳንትነት መንበር የተመለሱት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ ለስድስት ጊዜ ወደ ኤርትራ ለጉብኝት ማምራታቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነቱን በመሪዎቻቸው አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረመቻውን ተከትሎ ተቃውሞዋን ያሰማችው ሶማሊያ ድጋፍ ለማግኘት ፕሬዝዳንቷ ወደ ተለያዩ አገራት ተጉዘው ነበር።
ከስድስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል።
የመግባቢያው ሠነድ ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን የሚሰጥ ሲሆን፤ ሶማሊላንድ በምላሹ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል ሰፈር የሚውል የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚፈቅድ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ፣ ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና የሃርጌሳ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ድርጊት ነው ትላለች።
በዚህ ያልተገደበችው ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘቱን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ከግዛቷ እንደምታስወጣም ጭምር ገልጻለች።
በሁለቱ አገራት መካከል እየከረረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ የቱርክ መንግሥት አንካራ ላይ የሁለቱ አገራትን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች አገናኝቶ ቢያነጋግርም ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።












