የሐማስ ጦር አዛዥን በአየር ጥቃት መግደሏን እስራኤል አስታወቀች

የሐማስ ጦር አዛዥ መሐመድ ዴይፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሐማስ ጦር አዛዥ መሐመድ ዴይፍ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሐማስ ጦር አዛዥ መሐመድ ዴይፍን እስራኤል በጋዛ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. በፈጸመችው የአየር ጥቃት መግደሏን ጦሯ አስታወቀ።

ሃን ዩኒስ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ግቢ ውስጥ መሐመድ ዴይፍ በእስራኤል የአየር ጥቃት ዒላማ መደረጉ ተገልጿል።

የእስራኤል ጦር በወቅቱ ሌላኛው የሐማስ ጦር አዛዥ ራፋ ሳሌማህ በጥቃቱ መገደሉን ገልጾ፤ ነገር ግን የዴይፍ ዕጣ ፈንታን አላረጋገጥኩም ብሎ ነበር።

ሐማስ ስለዴይፍ መገደል እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።

እስራኤል ባለፈው መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ የተፈጸመባትን እና 1,200 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት ተጠያቂ ከምታደርጋቸው የቡድኑ መሪዎች መካከል ዴይፍ አንዱ ነው።

ይህ እስራኤል መሐመድ ዴይፍን መግደሏን የሳወቀችበትን መግለጫ ያወጣቸው የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ቴህራን ውስጥ እንዲሁም ፉዐድ ሹክር ቤይሩት ውስጥ በአየር ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ነው።

ጋዛ ውስጥ በ1965 (እአአ) የተወለደው መሐመድ ዴይፍ አል-ማስሪ በቅጽል ስሙ “አቡ-ኻሊድ” ወይም “አል-ዴይፍ” የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ መሪ ነበር።

በፍልስጤማውያን ዘንድ “ዋነኛው አንቀሳቃሽ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ እስራኤላውያን ደግሞ “የሞት መልዕክተኛ” ወይም “ባለዘጠኝ ነፍሱ ተዋጊ” በሚል ይጠራል።

ሞሐመድ ዴይፍ ጋዛ ውስጥ ከሚገኘው እስላማዊ ዩኒቨርስቲ ባዮሎጂ አጥንቶ በዲግሪ የተመረቀ ሲሆን፣ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ለትወና እና ለቲያትር ባለው ፍቅር እንዲሁም የኪነ ጥበብ ቡድን በማቋቋሙ ይታወቃል።

ዴይፍ ሐማስ መመሥረቱ ሲገለጽ ቡድኑን የተቀላቀለው በሙሉ ልብ አልነበረም። በ1989 (እአአ) ለሐማስ ወታደራዊ ቡድን ይሠራል ተብሎ በእስራኤል ባለሥልጣናት ከተያዘ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ለ16 ወራት ታስሮ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእስር ላይ በቆየበት ጊዜም ዴይፍ ከዛካሪያ አል-ሾርባጊ እና ከሳላህ ሺሃዲህ ጋር በመሆን ከሐማስ የተለየ የእስራኤል ወታደሮችን የሚማርክ ቡድን ለመመሥረት ተስማማ። ይህ እንስቃሴ ነው እንግዲህ ጎልብቶ አል-ቃሳም ብርጌድ ለመሆን የቻለው።

ዴይፍ ከእስር ከተፈታ በኋላ የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ ወታደራዊ ቅርጽ በመያዝ መንቀሳቀስ ጀመረ፣ ዴይፍም ከሌሎች የቃሳም መሪዎች ጋር በመሆን የቡድኑ ቀዳሚ መሥራች ለመሆን ቻለ።

ዴይፍ የሐማስ ተዋጊዎች ከጋዛ ተነስተው ወደ እስራኤል እንዲገቡ የሚያስችላቸውን የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻን የቀየሰው እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሮኬቶችን በአንድ ጊዜ የመተኮስ ሃሳብን ካራመዱት መካከል አንዱ ነው።

ከሁሉም በላይ በእስራኤል ከሚቀርቡበት ከባባድ ክሶች መካከል የሐማስ ቦምቦችን ይሰራ የነበረውን የያህያ አያሽ ግድያን ለመበቀል እንደ አውሮፓውያኑ 1996 መጀመሪያ ላይ 50 እስራኤላውያን የተገደሉባቸውን የአውቶብስ የቦምብ ጥቃቶች፣ እንዲሁም በ1990ዎቹ አጋማሽ ተማርከው የተገደሉ ሦስት እስራኤላውያን ጉዳይ ይጠቀሳሉ።

እስራኤል ዴይፍን በ2000 ላይ ይዛ አስራው የነበረ ቢሆንም፣ ሁለተኛው የፍልስጥኤማውያን አመጽ ሲቀሰቀስ ለማምለጥ ችሏል። ከዚያ በኋላም የት እንዳለ አይታወቅም።

አስካሁን የሚታወቁ የዴይፍ ሦስት ፎቶዎች አሉ። አንደኛው በጣም ያረጀ፣ ሁለተኛው ጭምብል አድርጎ እና ሦስተኛው ጥላውን የሚያሳዩ ናቸው።

ዴይፍ በጣም አደገኛ የሚባል የመግደል ሙከራ የተደረገበት በ2002 (እአአ) ነበር። በጥቃቱ ዴይፍ ተዓምር በሚባል ሁኔታ ቢተርፍም አንድ ዐይኑን አጥቷል።

እስራኤል ግን በጥቃቱ በተጨማሪ አንድ እጁን እና እግሩን ማታቱን እንዲሁም በተደጋጋሚ በተፈጸሙበት የግድያ ሙከራዎች ምክንያት የመናገር ችግር ገጥሞታል ትላለች።

በአውሮፓውያኑ 2014 የእስራኤል ሠራዊት ለ50 ቀናት የቆየ ጥቃትን በጋዛ ሰርጥ ላይ ባካሄደበት ጊዜ ዴይፍን ለመግደል ሳይችል ቢቀርም፣ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን ገድሏል።

የሐማሱ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ዴይፍ የሚለውን ስም የወሰደው “እንግዳ” ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው። ምክንያቱም የእስራኤልን ግድያ ለማምለጥ አንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ስለማይቆይ እና በየምሽቱ ለማደሪያነት የሚጠቀምብትን ስፍራ ስለሚቀያይር ነው።