በፊሊፒንስ አንድ ዲጄ በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, ACEBOOK / 94.7 GOLD FM CALAMBA
በፊሊፒንስ አንድ የሬዲዮ የሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ ተገደለ።
ጁዋን ጁማሎን (በዲጄ ስሙ ጆኒ ዎከር) የተገደለው በስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ ለአድማጮች እያጫዋተ ሳለ ነው።
የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ማርከስ የሬዲዮ ጋዜጠኛና ዲጄ ግድያን በብርቱ ቃል አውግዘዋል።
የፊሊፒንስ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ማኅበር እንደሚለው በ2022 ዓ/ም ብቻ አራት ጋዜጠኞች ተገድለዋል።
ማኅበሩ ይህን ግድያ ይበልጥ አስደንጋጭ የሚያደርገው ዲጄው መኖርያ ቤቱ ውስጥ በገነባው ትንሽዬ ስቱዲዮ ውስጥ ሳለ መገደሉ ነው።
ዲጄ ጆኒ ዎከር ሥርጭቱን በቀጥታ በፌስቡክ እያሰራጨ ሳለ ነበር አንድ ተጠርጣሪ ወደ ስቱዲዮው ሰተት ብሎ በመግባት ተኩሶ የገደለው።
የፊሊፒንስ ሚዲያዎች ከፖሊስ አገኘን ባሉት መረጃ መሠረት እንደዘገቡት ተጠርጣሪው ወደ ስቱዲዮ ዘልቆ መግባት የቻለው ለጥበቃዎች ‘’አስቸኳይ በቀጥታ ሥርጭት የሚነገር ማስታወቂያ አለኝ” ብሎ ዋሽቶ ነው።
ፖሊስ የሲሲቲቪ ቅጂዎች እጄ ገብተዋል ሲል ይፋ አድርጓል።
የዲጄ ጆኒ ዎከር ሥርጭት በ94.7 ጎልድ ሜጋ ካላምባ ኤፍ ኤም ፌስቡክ ገጽ ላይ የሚሠራጭ ሲሆን የፌስቡክ ገጹ 2ሺ 400 ተከታዮች አሉት።
ዲጄ ጆኒ ከተተኮሰበት በኋላ ባለቤቱ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ብታደርሰውም ሐኪሞች ጆኒ መሞቱን አርድተዋታል።
ፖሊስ በዲጄ ጆኒ ላይ ከዚህ ቀደም ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኛል ብሎ ሪፖርት እንዳላደረገ ገልጧል።
የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት በኤክስ ገጻቸው ‘’ፖሊስ ምርመራውን በጥልቀት እንዲያከናውንና ተጠርጣሪውን ከፍርድ እንዲያቀርብ” አዘዋል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ‘ፍሪደም ሐውስ’ “ፊሊፒንስ ዓለም ላይ ለጋዜጠኞች አደገኛ ከሚባሉ አገሮች አንዷ” ሲል ይመድባታል።












