ከኒውዮርክ ወደ ናይሮቢ በነበረ በረራ አንድ መንገደኛ ህይወቱ አለፈ

የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Public Domain

ከኒውዮርክ ወደ ናይሮቢ ለመብረር ተሳፍሮ የነበረ አንድ መንገደኛ ህይወቱ አለፈ።

ንብረትነቱ የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍሮ የነበረው መንገደኛ በበረራ ወቅት ታሞ መሞቱን ተከትሎ አውሮፕላኑ በረራውን ወደ ሞሮኮ ለማድረግ ተገዷል።

አየር መንገዱ እንዳስታወቀው ግለሰቡ የሞተው ሰኞ እለት ነው ብሏል።

የኬንያ አየር መንገድ በሰጠው መግለጫ አውሮፕላኑ ወደ ሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ የበረራ አቅጣጫውን እንዲቀይር የተደረገው በአውሮፕላን ማረፊያው የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች “ተሳፋሪው ምንም ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ እና መሞቱን ማረጋገጣቸውን” ተከትሎ ነው።

መንገደኛው የመተንፈስ ችግር እንደገጠመው የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። 

የሟቹ ቤተሰብ እንደተናገሩት ተሳፋሪው ከዚህ ቀደም ተደራራቢ የጤና እክል እንደነበረበት መናገራቸው ተዘግቧል።

በአውሮፕላን ውስጥ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች እንዳሳወቁት የመንገደኛው የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ መድከማቸውን ማየታቸውን ተከትሎ ስጋታቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።