የአሜሪካዋ ዲትሮይት ከተማ ምኩራብ ኃላፊ ተገድለው ተጣሉ

የፎቶው ባለመብት, ISAAC AGREE SYNAGOGUE/FACEBOOK

በአሜሪካ የዲትሮይት ከተማ ምኩራብ ፕሬዝደንት የሆኑት ሳማንታ ዎል ከቤታቸው አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ፓርክ ውስጥ ተገድለው ተጣሉ።

ፖሊስ እንደገለጸው ቅዳሜ ዕለት ከላፋየት ፓርክ አካባቢ በደረሰው ጥሪ መሠረት ወደ ሥፍራው ሲያቀና ግለሰቧ ሕይወታቸው አልፎ ነበር።

ፖሊስ እንደሚለው የምኩራቡ ፕሬዝደንት ቤታቸው ተገድለው ነው ፓርክ ውስጥ የተጣሉት።

ሥፍራውን በፖሊስ ውሻ ታግዞ ቢያስስም እስካሁን ግድያውን ማን እንደፈፀመውም ሆነ ለምን እንደተፈፀመ ፍንጭ እንዳላገኘ አስታውቋል።

ፖሊስ ጨምሮ እንደገለጠው ግድያው በፀረ-ሴማዊ ስሜት የተፈፀመ ስለመሆኑ የሚጠቁም መረጃ የለም።

የዲትሮይት ባለሥልጣናት ግለሰቧ ለከተማዋ ላበረከተችው አስተዋፅዖ ማስታወሻ ፕሮግራም አሰናድተዋል።

የሚቺጋን ግዛት አቃቤ ሕግ ዳና ኔሴል ኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ላይ በፃፉት መልዕክት “በሳም ግድያ እጅጉን ደንግጠናል ተረብሸናልም” ብለዋል።

የግዛቲቱ ሃገረ-ገዥ ግሬቸን ዊትመር ደግሞ ግድያው “ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ነው” ብለዋል።

“የብርሃን ምንጭ የሆነች፤ ለሕብረተሰቡ አሳቢ እና ሚቺጋን ነገ የተሻለ ሥፍራ እንድትሆን ጠንካራ የሠራች” ሲሉ ሃገረ-ገዢዋ ባወጡት መግለጫ ሳማንታን አስበዋል።

የይሁዳውያን ማሕበረሰብ ግንኙነት ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሳም ዱቢን በበኩላቸው ግለሰቧ፤ “ፈገግታ የማይለያቸው” ናቸው ሲሉ ዘክረዋቸዋል።

የዲትሮይት ፖሊስ ኃላፊ ጄምስ ዋይት ሳማንታ ዎል በምን ምክንያት ሊገደሉ እንደቻሉ ለማጣራት ምርመራ መከፈቱን አስታውቀዋል።

አክለው፤ የዲትሮይት ፖሊስ ክፍል መርማሪዎች ከፌዴራሉ ምርመራ ቢሮ [ኤፍቢአይ] ጋር በመጣር መረጃ አላቸው ያሏቸውን ሰዎች ቃለ-መጠይቅ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ማሕበረሰቡ ምርመራችንን እስክናጠናቅቅ እና የሕግ ሰዎች ሥራቸውን እስኪውኑ በትዕግስት እንዲጠባበቅ እጠይቃለሁ” ብለዋል።