የዩሮቪዥን ሽልማት ለዩክሬን ጦር ድሮን ለመግዛት ተሸጠ

የዩሮቪዥን ሽልማት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዘንድሮውን የዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድር ያሸነፈውና ካሉሽ ኦርኬስትራ የተሰኘው የዩክሬን ባንድ አባላት በውድድሩ ያሸነፉትን ዋንጫ በ900 ሺህ ዶላር መሸጣቸው ተሰምቷል።

ዋንጫውን የሸጡት ደግሞ ለዩክሬን ጦር ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ለመግዛት ነው ተብሏል።

የሙዚቃ ቡድኑ ከክሪስታል የተሰራውን ዋንጫ በፌስቡክ አማካይነት ነው በጨረታ ለሽያጭ ያቀረበው።   

የሙዚቃ ቡድኑ ጨረታ በጀርመኗ በርሊን ካካሄደው ኮንሰርት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ተካሂዷል። ኮንሰርቱም የተካሄደው ለዩክሬናውያን ወታደሮች የህክምና መገልገያዎችን ለማቅረብ የሚረዳ ገንዘብ ለማሰባሰብ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ14 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በርካቶችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በኮንሰርቱ ወቅት ንግግር ያደረገው የባንዱ አባል ኦሌህ ሲዩክ ሰዎች ጦርነቱን በቀላሉ እንዳይመለከቱትና ከ4 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች መሞታቸውን እንዲሁም ከ4 500 በላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሷል።

አክሎም ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዩክሬናውያን ተዋጊዎችም መገደላቸውን ተናግሯል።

"ሰላም እስከሚመጣ ድረስ ይህ ጉዳይ የሁሉም መገናኛ ብዙኃን የፊት ገጽ ላይ ሊወጣ ይገባል’’ ብሏል ኦሌህ ሲዩክ።

የሙዚቃ ቡድኑ የዩሮ ቪዥን ውድድርን ያሸነፈበት ‘ስቴፋኒያ’ የተሰኘው ሙዚቃ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ዩክሬናውያን ለተቃውሞ ሲወጡ የሚያቀነቅኑት ሆኗል።

ሴሪ ፕሪቱላ የተባለች የአንድ የዩክሬን ቴሌቪዥን ጣቢያ አቅራቢ ዋንጫውን በመሸጥ የተገኘው ገንዘብ ዩክሬን ውስጥ የሚመረቱ ‘ፒዲ-2’ የተባሉ ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመግዛት እንደሚውል መናገሯን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በዚህ ጦርነት ዩክሬንም ሆነ ሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) በበርካታ የጦርነት አውድማዎች እየተጠቀሙ ሲሆን ድሮኖቹም በጦር ግንባሮች ያለውን ሂደት እየቀየሩት ይገኛሉ።