ትራምፕ ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ በመግዛቷ የተጣለባት ታሪፍ ወደ 50 በመቶ ከፍ እንዲል አዘዙ

ዶናልድ ትራምፕ እና የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕንድ ከሩሲያ የነዳጅ ዘይት በመግዛቷ ተጨማሪ የ25 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልበት ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ።

ይህም ሕንድ ወደ አሜሪካ በምታስገባቸው ምርቶች ላይ የተጣለውን አጠቃላይ ታሪፍ ወደ 50 በመቶ ያሳድጋል።

አሜሪካ በተለያዩ አገራት ላይ ከጣለቻቸው ታሪፎች መካከል ይህ ከከፍተኞቹ የሚመደብ ነው።

በፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዙ አዲሱ ተመን በ 21 ቀናት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል።

የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት በሰጠው ምላሽ ዴልሂ ከሩሲያ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያላትን አቋም ግልፅ አድርጋለች።

እንዲሁም ታሪፉ "ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ስህተት እና ምክንያታዊ ያልሆነ" መሆኑን ገልጿል።

የሚኒስቴሩ አጭር መግለጫ አክሎም "በመሆኑም ዩናይትድ ስቴትስ በሕንድ ላይ ተጨማሪ ታሪፎች ለመጣል መምረጧ በጣም የሚያሳዝን ነው፤ ሌሎች በርካታ አገሮችም የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም እየመረጡ ነው" ብሏል።

"ሕንድ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ትወስዳለች" ሲል አክሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቀደም ሲል ሕንድ "በሩሲያ ጦር መሳርያ በዩክሬን ምን ያህል ሰዎች እንደሚገደሉ ግድ የላትም" በማለት ቀረጥ እንደሚጨምሩ አስጠንቅቀው ነበር።

ረቡዕ ዕለት ዋይት ሐውስ በሰጠው መግለጫ "የሩሲያ ፌዴሬሽን በዩክሬን የወሰደው እርምጃ በዩኤስ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ላይ ቀጣይነት ያለው ስጋት ስለሚፈጥር፣ ብሔራዊ ድንገተኛ አደጋን ለመቅረፍ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ብሏል።

ሕንድ የሩስያ ነዳጅ ዘይትን መግዛቷ፣ አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለመመከት የምታደርገውን ጥረት ያዳክማል ሲል ተናግሯል።

ዩናይትድ ስቴትስ የትኞቹ አገራት ከሩሲያ ነዳጅ እንደሚገዙ እንደምትወስን እና "እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ እርምጃዎችን የያዙ ምክረ ሃሳቦች ለፕሬዚዳንቱ እንደሚቀርቡ" አክሎ ገልጿል።

ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ በሩሲያ ትልቁ የወጪ ንግድ ሲሆን ከሞስኮ ግዙፍ ደንበኞች መካከል ቻይና፣ ሕንድ እና ቱርክ ይጠቀሳሉ።

በዓለም አቀፍ የሸቀጦች መረጃ ፕላትፎርም ኬፒለር መሠረት ሩሲያ ለሕንድ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት በመሸጥ ከ 35 በመቶ በላይ የአገሪቱን አጠቃላይ አቅርቦት ትሸፍናለች።

ለሮይተርስ የዜና ወኪል የተጋራ መረጃ እንደሚያሳየው ሕንድ ባለፉት ስድስት ወራት በቀን 1.75 ሚሊዮን በርሜል የሩሲያ ነዳጅ ዘይት ገዝታለች።

በዋይት ሐውስ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ላይ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ በሕንድ ላይ የተጣለው ታሪፍ ገና የመጀመሪያው ነው ብለዋል።

"ብዙ ተጨማሪ እና በጣም ብዙ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀቦችን ታያለህ" ብለዋል።

ሕንድ ላይ ተጨማሪ ታሪፍ የተጣለው ረቡዕ ዕለት የትራምፕ ከፍተኛ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በሞስኮ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማስፈን ያለመ ውይይት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ካካሄዱ በኋላ ነው።

አሁን የተጣለው ተጨማሪ ታሪፍ እንደ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጌጣጌጦች፣ የመኪና መለዋወጫዎች እና የባህር ውስጥ ምግቦች ባሉ ሕንድ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶች ላይ 50 በመቶ ቀረጥ የሚጨምር ሲሆን ይህም ዋነኛ የስራ ፈጠራ ዘርፎችን ይጎዳል።

ኤሌክትሮኒክስ፣ አይፎን እና መድሃኒቶች ለጊዜው ከታሪፍ ነጻ ሆነወ ይቆያሉ።

ዴልሂ ከዚህ ቀደም ትራምፕ ከሩሲያ በምትገዛው ነዳጅ ምክንያት የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ማስፈራራታቸውን ተከትሎ "ስህተት እና ምክንያታዊነት የጎደለው ነው" ብላ ነበር።

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ በግጭቱ መጀመሪያ አካባቢ ሕንድ ከሩሲያ ጋዝ እንድታስገባ "የዓለም አቀፍ የኃይል ገበያ መረጋጋትን ለማጠናከር" በሚል የማበረታቻ ይሁንታ ሰጥታ ነበር።

ሕንድ ከሩሲያ ማስመጣት የጀመረችው ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ የተለመዱት አቅራቢዎች ወደ አውሮፓ ፊታቸውን በማዞራቸው ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትራምፕ ታሪፍ ለመጣል የሚያደርጉት ማስፈራሪያ በዩክሬን ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አሜሪካ ጠቃሚ የንግድ አጋሮቼ ናቸው በምትላቸው አገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት እንድታቆም እስከ አርብ ድረስ ቀነ ገደብ የሰጡ ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ ነዳጅ ከአገሪቱ በሚገዙ አገራት ላይ 100% ታሪፍ፣ እንዲሁም ሩሲያ ላይ ቀጥተኛ ማዕቀብ ለመጣል ዝተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር የሁለተኛ ደረጃ ረታሪፍ ሲጥል ይህ የመጀመርያው አይደለም። ከዚህ ቀደም የቬንዙዌላ ነዳጅን የሚገዙ አገራትን ለመቅጣት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።

ሕንድ ዩናይትድ ስቴትስ ራሷ ከሩሲያ ጋር የንግድ ልውውጥ እያደረገች ተጨማሪ ታሪፍ በማስተዋወቋ ምክንያት የረዥም ጊዜ አጋሯን ወቅሳለች።

ምንም እንኳ ማዕቀብ እና ታሪፍ የተጣለባት ቢሆንም ባለፈው ዓመት ብቻ ዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ከሩሲያ ጋር 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ሸቀጦችን ተገበያይታለች።

ትራምፕ እና የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ከዚህ ቀደም ጓደኛ መሆናቸውን ሲገልፁ የነበሩ ሲሆን፣ በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አንዱ በሌላው አገር የፖለቲካ ሰልፎች ላይ ተገኝተዋል።

ነገር ግን ትራምፕ በኒው ዴልሂ እና በዋሽንግተን መካከል ያለውን ልዩነት በመጥቀስ ሕንድን በተጨማሪ ታሪፍ ከመቅጣት አላገዳቸውም።

የሕንድ የውጭ ንግድ ድርጅቶች ፌዴሬሽን ተጨማሪ ታሪፎችን ለመጣል መወሰኑን "እጅግ አስደንጋጭ" ሲል ገልጾ፣ ሕንድ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ምርቶች 55 በመቶውን እንደሚጎዳ ተናግሯል።

ታሪፉ በአሜሪካ ውስጥ የሕንድ ምርቶች በጣም እንዲወደዱ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ 40-50 በመቶ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ሊቀንስ ይችላል ሲል በዴልሂ መቀመጫወን ያደረገው ግሎባል ትሬድ ሪሰርች ኢኒሼቲቭ ገልጿል።

የድርጅቱ ኃላፊ አጃይ ስሪቫስታቫ "ሕንድ መረጋጋት አለባት፤ ቢያንስ ለስድስት ወራት የአፀፋ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ እና ከአሜሪካ ጋር ትርጉም ያለው የንግድ ድርድር ማድረግ በማስፈራሪያና አለመተማመን መቀጠል እንደማትችል ማሳወቅ አለባት" ብለዋል።