ሀንጋሪ ከሩሲያ ነዳጅ እንድትገዛ ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ትራምፕ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀንጋሪ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን የሩሲያን ነዳጅ እንዲገዙ ለመፍቀድ ማሰባቸውን ተናገሩ።
የሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም "ኦርባን ከሌላ ቦታ ነዳጅ ለማግኘት ስለሚቸገር" የሩሲያን ነዳጅ እንዲገዙ ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ኦርባን በዋይት ሀውስ ከትራምፕ ጋር ተወያይተዋል። የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው እንዳሉት፤ አገራቸው "ሙሉ እና ያልተገደበ የነዳጅ ግዢ" እንድታደርግ አሜሪካ "ማዕቀቦችን" አንስታለች።
አሜሪካ በሁለት የሩሲያ ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
በሁለቱ ግዙፍ ነዳጅ አምራቾች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ ማዕቀብ የተጣለው ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት እንድትደርስ ጫና ለማሳደር ነው።
ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዙ አገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል አሜሪካ ዝታለች።
ሀንጋሪ የባሕር በር ስለሌላት እና ሌሎችም የሎጅስቲክስ እንቅፋቶች ስለሚገጥሟት ነዳጅ ለማውጣትም ይሁን ለማግኘት እንደምትቸገር ትራምፕ ጠቅሰዋል።
በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም አንዳንድ የአውሮፓ አገራት መግዛት መቀጠላቸው "በጣም የሚረብሽ ነው" ብለዋል።
የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ከአውሮፓ መሪዎች መካከል ለትራምፕ ቅርብ የሚባሉት ናቸው።
የአውሮፓ አገራት ሩሲያ ላይ የሚጥሉት ማዕቀብ የአገራቸው የነዳጅ አቅርቦት ላይ ጫና እንደሚያሳድር ኦርባን ገልጸዋል።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦዎች መዘጋት "ፖለቲካዊ" ወይም "ፅንሰ ሐሳባዊ" ሳይሆን የአገሪቱን "ነባራዊ እውነታ" የሚወስን መሆኑን ገልጸዋል።
ኦርባን ከዚህ ቀደምም ሀንጋሪ ከነዳጅ ምርት ጋር በተያያዘ ሩሲያ ላይ ጥገኛ መሆኗን ይናገራሉ። የነዳጅ ግብይትን እንደምክንያት በመጠቀም ከሞስኮ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነትም ያስቀጥላሉ።
የነዳጅ አቅርቦት ጉዳይ በቀጣዩ ዓመት ምርጫ ለማሸነፍ ከሚጠቀሙባቸው ነጥቦች አንዱ ነው።
ለሀንጋሪ "ርካሽ የሩሲያ ነዳጅ ለማቅረብ" ቃል ሲገቡ ተደምጠዋል።
ትራምፕ በድጋሚ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ መሪዎች በዋይት ሀውስ ባደረጉት ውይይት የዩክሬንን ጦርነትም አንስተዋል።
ኦርባን ከፑቲን ጋር ሊነጋገሩ እንደሚችሉ የጠቆሙ ሲሆን ትራምፕም "ኦርባን ፑቲንን ያውቀዋል፤ ይረዳዋልም። በቅርቡ ጦርነቱን እንደምናስቆምም ያምናል" ብለዋል።
ኦርባን በበኩላቸው ሁለት አገራት ብቻ የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
"ሌሎች አገራት ጦርነቱ ቢቀጥል ይመርጣሉ። ዩክሬን ተዋግታ እንደምታሸንፍ የሚያምኑ ቢኖሩም ከእውነታው የራቀ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ "ዩክሬን ጦርነቱን ታሸንፋለች ብለህ አታምንም?" ሲሉ የሀንጋሪውን ፕሬዝዳንት ጠይቀዋል። ኦርባንም "ተዓምር ሊፈጠር ይችል ይሆናል" በማለት መልሰዋል።
ትራምፕ የአውሮፓ ሸቀጦች ላይ በጣሏቸው ታሪፎች ምክንያት የሀንጋሪ ምጣኔ ሀብት ተዳክሟል። በተለይም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎች ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት መሪዎች ከስደተኞች ፖሊሲ እንዲሁም ከዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት መስፈን ጋር በተያያዘ ከኦርባን ጋር አይስማሙም።
ትራምፕ ግን "ኦርባን በስደተኞች ጉዳይ ያለው አቋም ትክክለኛ ስለሆነ" የአውሮፓ መሪዎች አክብሮት እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።















