ብሩስ ዊልስ የፊቱን ገጽታ መብት ሸጧል መባሉን አስተባበለ

የብሩስ ዊልስ ወኪል የፊልም ኮከቡ የፊቱን ገጽታ መብት እንደሸጠ የሚገልጹ ዘገባዎችን አስተባብሏል።
ባለፈው ሳምንት ዊልስ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው በተባለለት ውል የፊቱን ገጽታ ዲፕኬክ ለተባለ የዲፕ ፌክ (የሰውን ገጽታ እና ድምጽ ለሚያስመስል) ኩባንያ መሸጡ በስፋት ተዘግቧል።
የተዋናዩ ቃል አቀባይ ግን ከኩባንያው ጋር ምንም አይነት ሽርክና ወይም ስምምነት እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግሯል።
የዲፕኬክ ተወካይም ዊልስ ብቻ በራሱ ፊት ላይ መብት እንዳለው ተናግረዋል።
ዊልስ ንግግርን የሚጎዳ አፋሲያ የተባለ በሽታ እንዳለበት ከታወቀ በኋላ በመጋቢት ወር ትወና ማቆሙን አስታውቋል።
ዲፕፌኮች ሰው ሠራሽ አስተውሎዎችን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እና የማሽን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ብዙ ጊዜ የታዋቂ እና ፖለቲከኛ ሰዎችን እውነተኛ የሚመስሉ ቪዲዮዎችን ይሠራሉ።
ከአሁን በኋላ መሥራት ለማይችሉ ተዋናዮች ቴክኖሎጂው ጨዋታ ቀያሪ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ዴይሊ ሜይል መስከረም 27 እንዳስነበበው በዊልስ እና በዲፕኬክ መካከል ስምምነት መደረሱን ዘግቧል።
"የሁለት ጊዜ የኤሚ አሸናፊው ብሩስ ዊልስ የምስል መብቱን ለዲፕኬክ በመሸጡ አሁንም በፊልሞች ላይ መታየት ይችላል" ሲል አስነብቧል።
ዘገባውን ቴሌግራፍ እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃንም ተቀባብለውታል።
"ብሩስ ዊልስ የራሱን ‘የዲጂታል መንታ' ለስክሪን ጥቅም ላይ እንዲውል መብቱን የሸጠ የመጀመሪያው የሆሊውድ ኮከብ ሆኗል” ሲል ቴሌግራፍ ጽፏል።
አውነታውን ከዚህ የተለየ ነው።
እውነቱ የቱ ነው ከተባለ ባለፈው ዓመት የብሩስ ዊሊስ ዲፕ ፌክ ሜጋፎን ለተባለው የሩሲያ የቴሌኮም ኩባንያ ማስታወቂያ መስሪያነት ጥቅም ላይ ውሏል።
ለማስታወቂያው ጥቅም ላይ የዋለውን ቴክኖሎጂ የተፈጠረው በዲፕኬክ ነው። ኩባንያው በሰው ሠራሽ አስተውሎ ዲፕ ፌክ እንደሚያዘጋጅ ይገልፃል።
ዲፕኬክ በማስታወቂያው ላይ ከዊሊስ ቡድን ጋር በቅርበት መስራቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በእርግጠኝነት የምንናገረው ነገር ቢኖር ዲጂታል መንትያውን ለመስራት ፈቃዱን (እና ብዙ ቁሳቁሶችን) መስጠቱን ነው" ብሏል።
ኩባንያው ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የታዋቂ ሰዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ታሪካዊ ሰዎች ስብስብ ያሉበት ልዩ ቤተ-መጽሐፍት እንዳለው ተናግሯል።
የዊልስ ወኪል ለቢቢሲ እንደተናገረው "ብሩስ ከዲፕኬክ ኩባንያ ጋር ምንም አይነት ሽርክና ወይም ስምምነት የለውም" ብሏል።
ዲፕኬክም በመግለጫ ላይ ኩባንያው የብሩስ ዊልስ ገጽታ መብትን እንደገዛ የሚገልጹት ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸው ብሏል።
የኩባንያው ተወካይ "መብቶች የሚለው ቃል ስህተት ነው… ብሩስ ለማንም ሰው ምንም አይነት መብት አልሸጠም። ይህ የእሱ ናቸው” ብሏል
ግራ መጋባቱ ቴክኖሎጂው ምን ያህል አዲስ እንደሆነ እና በጉዳዩ ላይ ግልጽ ህጎች አለመኖራቸውን ያሳያል።












