ቻይና በምግብ ዘይት መበከል ቅሌት እየተናጠች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና መንግሥት የነዳጅ መጫኛ ታንከሮች በአግባቡ ሳይጸዱ የምግብ ዘይት ለማጓጓዝ ጥቅም ላይ በመዋላቸው ዘይቱ በመርዛማ ኬሚካሎች ተበክሏል የሚለውን ውንጀላ እንደሚያጣራ አስታወቀ።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የምግብ መበከል ስጋት እንዳላቸው የሚገልጹ ጉዳዮች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚያገለግሉ መጫኛ ታንከሮች በትክክል ሳይጸዱ እንደ የምግብ ዘይት እና ሽሮፕ ያሉ የምግብ ምርቶችን ይዘው ተገኝተዋል ሲል መንግስታዊው ቤጂንግ ኒውስ ዘግቧል።
ጋዜጣው ዋቢ ያደረገው አንድ አሽከርካሪ ኢንዱስትሪው ውስጥ የምግብ ዘይትን በተበከለ የነዳጅ ታንከሮች ማጓጓዝ በጣም የተለመደ መሆኑን “የአደባባይ ሚስጥር” ሲል ገልጾታል።
ጉዳዩ የቻይና መንግሥት የምግብ ደህንነት ደረጃዎችን የማስከበር አቅም ላይ ህዝቡ የመተማመን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ሆኗል ተብሏል።
ውዝግቡ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።
በዌቦ (የቻይናው ኤክስ በመባል ይታወቃል) ላይ ስለቅሌቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጽሁፎች ያሉ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እይታዎችንም አግኝተዋል።
"የምግብ ደህንነት በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ነው" የሚል አንድ አስተያየት ከ8 ሺህ ጊዜ በላይ ተወዳጅነት አግኝቷል።
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “እንደ ተራ ሰው በዚህ ዓለም መኖር በራሱ አስደናቂ ነገር ነው” ብሏል።
ብዙዎች ጉዳዩን ከ2008 የሳንሉ ወተት ቅሌት ጋር አነጻጽረውታል። በወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሜላሚን የሚባል የኢንዱስትሪ ኬሚካል ያለበት የዱቄት ወተት ጠጥተው 300 ሺህ የሚያህሉ ህጻናት ታመው ቢያንስ ስድስቱ ሕይወታቸው አልፏል።
"ይህ ከሳንሉ ቅሌት በጣም የከፋ ነው። በአንድ መግለጫ ብቻ ሊፈታ አይችልም" ሲል ሌላ ዌቦ ተጠቃሚ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ቻይና ውስጥ ታንከሮች ለተለያዩ ምርቶች ባለመለየታቸው ምክንያት የድንጋይ ከሰል ዘይቶችን ካጓጓዙ በኋላ የምግብ ምርቶችን በቀጥታ የማጓጓዝ ዕድል አላቸው።
መንግሥታዊዎቹን ሲኖግሬይን እና ሆፕፉል ግሬይን እና ኦይል ግሩፕን ጨምሮ በርካታ ዋና ዋና የቻይና ኩባንያዎች ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
የምግብ ደህንነት ደንቦች በትክክል መተግበራቸውን እያጣራ መሆኑን ሲኖግሬይን ተናግሯል።
ህጎቹን ጥሰው የተገኙ ማናቸውንም የጭነት ታንከሮች በፍጥነት እንደሚያግድ ኩባንያው አስታውቋል።
የሆፕፉል ግሬይን “የራሱን ፍተሻ” እያካሄደ መሆኑን ተወካዩ በመንግሥት ለሚተዳደረው ግሎባል ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የቻይና መንግሥት በበኩሉ የምግብ ደህንነት ባለስልጣናት በቀረው ክስ ላይ ምርመራ እንደሚያካሂዱ አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ ኩባንያዎችን እና ግለሰቦችን እንደሚቀጣም ቃል ገብተዋል።
የምርመራ ውጤቱንም በፍጥነት ይፋ እንደሚያደርግ አክሏል።
"ህገወጥ ኢንተርፕራይዞች እና የሚመለከታቸው ተጠያቂ አካላት በህጉ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት ይጣልባቸዋል" ሲል መንግስታዊው ሲሲቲቪ ዘግቧል።
የሄቤይ እና የቲያንጂን ግዛቶችም ጉዳዩን እየተመለከቱት መሆናቸውን ተናግረዋል።












