ከዓለም የተነጠለችው ሰሜን ኮሪያ ዜጎቿን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል 'ትኩስ ነገር ጠጡ' አለች

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ክትባት ለሕዝቧ ያልሰጠችው ሰሜን ኮሪያ ያለ ምንም መድኃኒት ከወረርሽኙ ጋር ግብግብ ገጥማለች።

ወረርሽኙ በመላው ዓለም ሲሰራጭ አገሪቷ ድንበሯን መዝጋቷ ይታወሳል።

የመድኃኒት ድጋፍም አልፈልግም ብላለች።

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ባህላዊ መድኃኒትን እየመከሩ ነው።

የገዢው ፓርቲ ጋዜጣ ሮዶንግ ሲሙን ባወጣው ዘገባ፣ እምብዛም በሽታው ያልጸናባቸው ሰዎች ትኩስ ነገር በመጠጣት እንዲያገግሙ መክሯል።

በዋነኛነት የዝንጅብል ወይም የማር ሻይ እንዲጠጡ ነው ዜጎች የተመከሩት።

ጉሮሮ መከርከር፣ ሳል እና ውሃ ጥምን ለማስታገስ ሻይ ፍቱን እንደሆነ መገናኛ ብዙኃኑ አስተዋውቀዋል።

ዝንጅብል ሕመምን እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃኑ ይህን ይበሉ እንጂ እነዚህ ባህላዊ መድኃኒቶች በሽታውን አያክሙም።

በመንግሥት የሚተዳደረው ቴሌቭዥን ጣቢያ ከሰሞኑ ያነጋገራቸው ጥንዶች፣ ጠዋትና ማታ ውሃ በጨው በጥብጦ መግሞጥሞጥን መክረዋል።

በሺህ ቶን የሚለካ ጨው ወደ ፒዮንግያንግ ተልኮ ፀረ ባክቴርያ ለመሥራትም ታቅዷል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ውሃና ጨው በጥብጦ መግሞጥሞጥ ጉንፋን የሚያሲዘውን ቫይረስ ቢከላከልም፣ ኮሮናቫይረስን ስለማስወገዱ መረጃ የለም።

አንድ ጥናት እንደጠቆመው፣ የአፍ መታጠቢያ ቫይረሱን ቤተ ሙከራ ውስጥ ለመግደል ይረዳል።

ሆኖም ግን ሰዎች በየቤታቸው ቢጠቀሙት ውጤታማ አይሆንም።

ቫይረሱ በአፍና አፍንጫ በኩል ነው የሚገባው። መግሞጥሞጥ ደግሞ በአፍ የሚገባው ቫይረስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ቫይረሱ አንዴ ሰውነት ውስጥ ከገባ በከፍተኛ ፍጥነት ይሰራጫል።

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዜጎች እንደ አይቡፕሮፊን እና አሞክሲሲሊን ያሉ ሕመም ማስታገሻዎች እንዲወስዱም መክረዋል።

እነዚህ ሙቀትን ለመቀነስ፣ ራስ ምታትን ለማስወገድና የጉሮሮ መከርከርን ለማስታገስ ቢረዱም፣ የቫይረሱን ስርጭት አይገቱም።

ባክቴርያን ለመከላከል የተሠሩ መድኃኒቶች ቫይረስን ለማስወገድ አይመከሩም።

እንዲሁ ሕመም ማስታገሻ መውሰድ ለሌላ ሕመም ይዳርጋል።

በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ሕመም እንዳይጸናባቸው መውሰድ ካለባቸው መድኃኒቶች መካከል ፓክሎቪድ፣ ሞልኑፒራቪር እና ረምደስቪር ይጠቀሳሉ።

በሰሜን ኮርያ በገጠራማ አካባቢዎች በነጻ ሕክምና ሲሰጥ፣ ልዩ ሕክምና በከተማ የመንግሥት ሆስፒታሎች ይሰጣል።

ሆኖም ግን በአገሪቱ የተጣሉ ማዕቀቦችና የአየር ንብረት ለውጥ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት አሽመድምዷል።

አገሪቱን ከዓለም ነጥሎ መዝጋቱም ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የመድኃኒት፣ የሕክምና ቁሳቁስና የባለሙያዎች እጥረትም አሳሳቢ ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት አምና ባወጣው ሪፖርት፣ ክትባት እንዲሁም መድኃኒትም በተገቢው ደረጃ ወደ አገሪቱ እንዳልገባ ጠቁሟል።

ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ የሸሹ እንደሚሉት፣ ለሕክምና እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።

መድኃኒት ለገዢው ፓርቲ አባላትና የቅርብ ሰዎቻቸው በቅድሚያ እንደሚሰጥም ይናገራሉ።

የአገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ ግን የመድኃኒት አቅርቦትን ለማስፋት እየተሠራ ነው ይላል።

በመላው ዓለም የኮቪድ-19 ክትባት የሚያከፋፍለው ኮቫክስ ጥምረት፣ አምና ለሰሜን ኮሪያ 3 ሚሊዮን ቻይራ-ሠራሽ ክትባቶች ለመለገስ ቢጠይቅም፣ አገሪቱ አልተቀበለችም።

ከሰሞኑ ግን ሰሜን ኮሪያ ሦሰት አውሮፕላኖች መድኃኒት ይዘው እንዲመለሱ ወደ ቻይና መላኳ ተሰምቷል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "የሚወስዱት የሕክምና ቁሳቁስ ቫይረሱን ለመከላከል የተዘጋጁ መድኃኒቶችን ባያካትትም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን" ብሏል።