በዩኬ ኮቪድ-19 በህሙማን ላይ የቆየበት ረጅሙ ጊዜ ከ16 ወር በላይ መሆኑን ምርመራዎች አመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም ሐኪሞች ኮቪድ-19 በህሙማን ላይ የቆየበትን ረጅም ጊዜ መዝገበዋል።
ሐኪሞቹ በኮቪድ-19 ተይዘው ሕክምና ያደረጉላቸው ህመምተኛ ከቫይረሱ ነጻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለ16 ወራት ወይም ለ505 ቀናት እንደቆዩ ምርመራዎች እንዳመለከቱ ገልጸዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰው እኝህ ግለሰብ ሌላ ተጓዳኝ በሽታዎች የነበሩባቸው ሲሆን እአአ በ2021 ሆስፒታል ውስጥ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።
እኝህ ግለሰብ ለ16 ወራት ያህል በተመረመሩ ቁጥር ቫይረሱ ይገኝባቸው ነበር።
የለንደን የሕክምና ባለሙያዎች ለረጅም ጊዜ በቫይረሱ ተይዞ መቆየት እምብዛም የተለመደ አይደለም ይላሉ።
አብዛኛው ሰው በተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም ከቫይረሱ ነጻ ይሆናሉ። ነገር ግን ቀደም ሲል የተጠቀሱት ግለሰብ የነበራቸው በተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም እጅግ የተዳከመ ነበር።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደዚህ ያሉ ስር የሰደዱ የሰውነት መቆጣቶችን ስለኮቪድ ያለን ግንዛቤ እና ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ለማሻሻል ጥናት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ ብለዋል።
ህመምተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 የተያዙት በ2020 መጀመሪያ ላይ ነበር። የበሽታው ምልክትም የነበራቸው ሲሆን በፒሲአር ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ከ72 ሳምንታት ለሚበልጥ በርካታ ጊዜ ለመደበኛ ምርመራ እና ለእንክብካቤ ሆስፒታል ሲገቡ እና ሲወጡ ነበር።
በአጠቃላይ ለ50 ጊዜ ያህል ምርመራ አድርገው ከቫይረሱ ነጻ አለመሆናቸው በምርመራ ተረጋግጧል።
የኪንግስ ኮሌጅ ለንደን እና ጋይስ ኤንድ ሴንት ቶማስ ኤንኤችኤስ ፋውንዴሽን ትረስት ሐኪሞች እንዳሉት ግለሰቡ በተደጋጋሚ በቫይረሱ የተያዙ ሳይሆን አንድ ጊዜ ተይዘው ለረዥም ጊዜ ከቫይረሱ ሳያገግሙ መቆየታቸውን ዝርዝር የሆነ ላብራቶሪ ምርምራ ትንታኔ አሳይቷል።
ህመምተኛው የፀረ ቫይረስ መድሃኒቶች ከወሰዱ በኋላ እንኳን ከበሽታው ማገገም አልቻሉም ነበር።
ይህ አንድ ግለሰብ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተረጋግጦ ምልክቶቹ ከማይጠፉበትና በቫይረሱ ለረዥም ጊዜ ተይዞ መቆየት ጋር የተለየ ነው።
በሕክምና ጉባዔ ላይ ስለግኝቶቹ ከሚያቀርቡት ሐኪሞቹ አንዱ በአውሮፓ ኮንግረንስ ክሊኒካል ማይክሮባዮሎጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሉኬ ብላግዶን ስኔል ናቸው።
ዶክተር ሉኬ "ከጉሮሮ የሚወሰድ ናሙና ምርመራ ይደረግ ነበር። ግለሰቡ ሁል ጊዜ በተመረመሩ ቁጥር ከቫይረሱ ነጻ አለመሆናቸውን ያሳይ ነበር።
ህመምተኛው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ኖሯቸው አያውቅም። እናም ይህ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በሽታ እንደሆነ መናገር እንችላለን። ምክንያቱም የቫይረሱ ዘረ መል ላይ ያደረግነው ተከታታይ ምርመራ ቫይረሱ በህመምተኛው ላይ የተለየ እና ወጥ የሆነ እንደሆነ አመላክቷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶክተር ሉኬ "ሰዎች ለረጅም ጊዜ በቫይረሱ ተይዘው ሲቆዩ ቫይረሱ ከሰውነታቸው ጋር ይላመዳል። ይህም አዳዲስ ዝርያዎችን ለመከላከል አቅም እንዲያዳብሩ ሊያግዝ ይችላል" ብለዋል።
ምርመራ ካደረጉላቸው ዘጠኝ ታካሚዎች መካከልም አንዳቸውም በሌላ የቫይረስ ዝርያ አለመያዛቸውን ዶክተር ሉኬ ተናግረዋል።
ስር በሰደደ ኢንፌክሽን የተያዘ ሰው ቫይረሱን ለሌሎች ላያስተላልፍ እንደሚችልም ዶክተር ሉኬ አክለዋል።












