የዓለም ጤና ድርጅት 65 በመቶ የሚሆነው አፍሪካዊ ለኮሮናቫይረስ ተጋልጧል አለ

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት አፍሪካውያን ለኮቪድ-19 ቫይረስ መጋለጡን አሳውቋል።

በአህጉሪቱ ምንም አይነት ምልክት ሳይታይባቸው በቫይረሱ ግን የተያዙ ሰዎች ቁጥር በመበራከቱ ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ ተይዟል ተብሎ እንዳልተመዘገበ አንድ ጥናት አመላክቷል።

ይህ ደግሞ በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በይፋ ከሚታወቀው በ97 እጥፍ መብለጡን የሚያሳይ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ዶክተር ማሺዲሶ ሞኢቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሁኑ ላይ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር በአህጉሪቱ ካለው ትክክለኛ ቁጥር አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል።

ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር በኮሮናቫይረስ የሚያዙ አፍሪካውያን የሚያሳዩት የሕመም ምልክት ቀለል ያለ ነው።

በአህጉሪቱ በአንፃራዊ ሲታይ እንደ ስኳር፣ የደም ግፊት እና ሌሎች ከኮቪድ-19 የከፋ ሊያደርጉ የሚችሉ በሽታዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን ወረርሽኙ በአፍሪካ እንደሌሎች አህጉሮች እንዳይበረታ አድርጎታል።

አፍሪካ አብዛኛው ሕዝቧ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በአንጻራዊነት ኮቪድ-19 በአህጉሪቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል ሌላኛው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።