የጀርባ አጥንቱ እና ነርቩ ከጥቅም ውጪ የሆነን ሰው ቆሞ እንዲራመድ ያስቻለ ተአምራዊ ሕክምና

ከጀርባ አጥንቱ ክፉኛ መጎዳት በኋላ ህበለ ሰረሰሩ (ነርቭ) ከጥቅም ውጪ ሆኖ የሰነበተ አንድ ግለሰብ እንደ ጤነኛ ሰው ቆሞ መራመድ ችሏል።
ይህ የሆነው በተአምር ሳይሆን በሳይንስ ነው።
በሰው ልጅ ታሪክ የመጀመሪያ የተባለው ይህ ሳይንሳዊ እመርታ እውን የሆነው በስዊዝ የተመራማሪዎች ቡድን ነው።
ይህን ግኝት በሰው ልጅ ታሪክ ፈር ቀዳጅ ያሰኘው ህብለ ሰረሰሩ ከጥቅም ውጪ የሆነን ሰው ለአፍታም ቢሆን በድጋሚ ቆሞ መራመድ ማስቻሉ ነው።
ይህ አዲስ ግኝት ከዚህ ግለሰብ በተጨማሪ ሌላ ሰው በድጋሚ ቆሞ መሄድ ብቻ ሳይሆን የልጅ አባት እንዲሆን አስችሎታል።
ይህም በዝነኛው የኔቸር የሕክምና ግኝቶች መሰነጃ ጆርናል ላይ ታትሟል።
ሚሸል ሮካቲ የሞተር ሳይክል ሲጋልብ ነበር አደጋ ደርሶበት ከአምስት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ ሽባ የሆነው።
ህብለ ሰረሰሩ ከጥቅም ውጭ በመሆኑም እግሩ አካባቢ ምንም ስሜት አይሰማውም ነበር። በአጭሩ እግሩ ከእርሱ ጋር ይሁን እንጂ ቀሪው ሰውነቱና እግሩ ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም።
አሁን ግን የእግሩን ስሜቶች እያዳመጠ፣ እየተረዳ እግሩን ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው ለአጭር ጊዜ ቆሞ መራመድ ችሏል።
ይህ እንዲሆን የተቻለው ኤሌክትሪካል ተከላ በቀዶ ሕክምና በህብለ ሰረሰሩ በኩል መገጠም ስለተቻለ ነው።
ይህ የኤለክትሪካል ተከላ በጀርባ አጥንት በኩል ሲገጠም ተቋርጦ የነበረው ከአእምሮ ወደ እግር በህብለ ሰረሰር ነርቮች በኩል ይላክ የነበረው መልዕክት በድጋሚ መሥራት ይጀምራል።
አንድ ሰው ቆሞ መሄድ የሚችለው በህብለ ሰረሰሩ የጫፍ ነርቮች ሥራሥር በኩል አእምሮና ከወገብ በታች ያለው ክፍል መልዕክት መቀባበል ስለቻሉ ነው።
የህብለ ሰረሰር ጉዳት ሽባ የሚያደርገውም ይህ የመልዕክት ልውውጥ ስለሚቋረጥ ነው።

ከዚህ የአሌክትሮኒክ ሕክምና ስኬት ጀርባ ካሉት ተመራማሪዎች አንዱ፣ ይህ አዲስ ግኝት እጅግ ውስብስብ እንደሆነና ለህብለ ሰረሰር መድቀቅ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሚሆን እንዳልሆነ አብራርተው፤ ሆኖም ግን ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሕይወት በማቃናት ረገድ በሰው ልጅ ታሪክ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ሙሉ በሙሉ ሽባ የነበረው ሚሼልን ሕክምናው በሚደረግበት ቤተ ሙከራ ሆኖ እንደተናገረው "ይህ ቴክኖሎጂ ለእኔ የመጣ ውድ የሕይወት ስጦታ ነው" ብሏል።
"አሁን መቆም፣ መራመድ፣ የፈለኩበት መሄድ፣ ደረጃ መውጣትና መውረድ ችያለሁ፤ ዳግም ሙሉ ሰው እያደረገኝ ነው" ሲል አዲሱ ሕክምና ሕይወቱን እንዴት እንደለወጠው አብራርቷል።
በእርግጥ ቴክኖሎጂው ብቻ አይደለም ይህን ጣሊያናዊ ለዚህ ስኬት ያበቃው።
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሕይወት ለመመለስ ቁርጠኛ ፍላጎትና ተስፋ ያለመቁረጥ ጠንካራ ስሜት ይዞ ነበር የቆየው።
"አደጋው ሳይመጣ በፊት ቦክስ እሠራ ነበር። የአካል ማጎልበቻ እንቅስቃሴ ማዕከል ውስጥ ብዙ ጊዜ አጠፋ ነበር። ሆኖም ከአደጋው መልስ የምወደውን ነገር ሁሉ ማድረግ ተሳነኝ። ይሁንና ድባቴ ውስጥ እንድገባ አልፈቀድኩም። ይህን ችግር እወጠዋለሁ ብዬ ቆራጥ ውሳኔ ላይ ደረስኩ።"
ሚሸል ከአደጋው ያገገመበት ፍጥነት ኒውሮሰርጅኖችን ጭምር አስደንቋል።
ከእነዚህ መካከል ፕሮፌሰር ጆሰሊን በሎች ይገኙበታል። በሚሸል ህብለ ሰረሰር ውስጥ ይህን አዲስ የኤሌክትሮዶስ የነርቭ ፋይበር (የነርቭ ሥራሥሮች) ያስገቡለት ተመራማሪ ናቸው።
"እጅግ ነው የተደነቅኩት፤ የማይታመን ተስፋና ጥንካሬ ያለው ሰው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ አዲስ ሙከራ ዶ/ር ራም ሐሪሐራንም በማማከር ተሳትፈውበታል። እሳቸው በሼፊልድ ኖርዘርን ጄኔራል ሆስፒታል አማካሪ ናቸው።
"ሐኪሞቹ ያደረጉት ነገር በሰው ልጅ ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ነገር ነው። ህብለ ሰረሰር ውስጥ የኤሌክትሮዶስ ነርቭ ሥራሥሮችን በመቀጣጠል የጀርባ አጥንት ዳግም ወደ ሥራው እንዲመለስ ማድረግ ታይቶም ተሰምቶም የሚታወቅ ነገር አይደለም" ብለዋል።
ዶ/ር ራም ከዚህ በኋላም በዚህ ጥናት ላይ ሰፊ ሥራ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። "ያ ከሆነ ብቻ ነው ይህ ሕክምና እውነትም ተአምራዊ ነው ማለት የምንጀምረው።"
በህብለ ሰረሰር ውስጥ የተገጠሙ ሰው ሠራሽ ነርቮች ከአንጎል ወደ እግር መልዕክት መላካቸው በእርግጥም አስደናቂ የሕክምና ስኬት ነው።
ብዙ ሰዎች ሽባ የሚሆኑት እነዚህ ነርቮች ከጥቅም ውጪ ሲሆኑ ነው።
የሚሸልን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ምንም ዓይነት ስሜት እግሩ አካባቢ አይሰማውም ነበር። ምክንያቱም ህብለ ሰረሰሩ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ስለቆየ።

አሁን ሰው ሠራሽ የኤሌክትሮኒክ ሕክምናው ያደረገው ቀጥታ ወደ እግሩ መልዕክትን ከአንጎል ተቀብሎ መላክ።
"አሁን ይህ ሙከራ አስተማማኝ እንደሆነ ለማመን በሌሎች የህብለ ሰረሰር ታማሚዎች ዘንድም ሕክምናው እንደሚሠራ ማረጋገጥ ይኖርብናል" ይላሉ።
እስከ አሁን ድረስ ዘጠኝ ሰዎች ይህን ተመሳሳይ ሕክምና ያገኙ ሲሆን ሁሉም ዳግም መራመድን በተወሰነ ደረጃ አሳክተዋል።
ሆኖም አሁን በዋናነት ሁሉም ዘመናዊውን ሕክምና ያገኙ ሰዎች መራመድ ሲፈልጉ በየጊዜው ለመራመድ አይጠቀሙበትም።
ይልቅ ሰውነታቸውን ዳግም መራመድን ለማለማመድ ነው እየተጠቀሙበት ያሉት። ጡንቻዎቻቸው ዳግም ሥራቸውን እንዳይረሱ ለማድረግ ጭምር አግዟቸዋል።
ዴቪድ ሜዚ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።
ልክ እንደ ሚሸል ሁሉ መራመድ ችሎ ነበር።
በኋላ ላይ እንዲያም አደጋው ከደረሰበት በኋላ አሳካዋለሁ ብሎ ያላሰበውን ነገር አሳክቷል።
ከሴት ጓደኛው ጄኒን ሴት ልጅ አግኝቷል።
ሴት ልጁ ዞዪ ትባላለች። አሁን አንድ ዓመቷ ነው።
"እሷ ከአባቷ ጋር ስትሆን በልጅ የድክድክ መለማመጃ ላይ ሆና አባቷም መራመድን እየተለማመደ ይሽቀዳደሙ ነበር" ትላለች እናት ጄኒን።
"ደስ የሚል ጊዜ ነበር፤ እኔም ለመራመድ ትግል እገጥማለሁ፤ የአንድ ዓመት ልጄ ዞዪም እንዲሁ፤ ሁለታችንም አንድ የሚያደርገን ለመራመድ ተለማማጅ መሆናችን ነበር" ሲል ስሜቱን አጋርቷል፤ አባት።
ፕሮፌሰር ግሪጎይር ኮርቲን ይህን አዲስ ሕክምና የመሩ ሊቅ ናቸው።
"አዲሱ ሕክምና ገና ሙከራ ላይ ነው። ብዙ ይቀረዋል። ሽባ የሆኑ ሰዎችን በድጋሚ መራመድ እንዲችሉ ለማድረግ ገና ብዙ ውስንነቶች አሉበት። ይህ የህብለ ሰረሰር ሕክምና አይደለም። ይህ ሽባ የሆኑ ሰዎችን ሕይወታቸውን ለማሻሻል የተደረገ አዲስ ሙከራ እንጂ ሌላ አይደለም" ብለዋል።
"ሽባ የሆኑ ሰዎች ዳግም ቀና እንዲሉ ጉልበት የሚሰጥ ነው። መቆምና መራመድ መጀመር ከቻሉ ይህ ትልቅ ሞራል ይሰጣቸዋል" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
ህብለ ሰረሰሩ የተሰበረ ሰው ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሊመለስ የሚችልበት ዕድል ለጊዜው የተመናመነ ነው።
ምናልባት ከመቅኔ የህብለ ሰረሰር ህዋሳት ዳግም እንዲወለዱና እንዲያቆጠቁጡ ማድረግ ከተቻለ ተስፋ ሊኖር ይችላል።
እስከዚያ ግን ይህ የኤሌክትሮዳይስ ሕክምና ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተመዝግቧል።















