ፌስቡክ ማኅበራዊና ፓለቲካዊ ቡድኖችን እንድንቀላቀል መጠቆም ሊያቆም ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ የተለያዩ ማኅበራዊና ፓለቲካዊ ቡድኖችን እንዲቀላቀሉ የሚጠቁም መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚያቆም አስታወቀ።
ይህ ውሳኔ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ የሚያዩትን ፓለቲካ ነክ ይዘት ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው።
የአሜሪካ ምርጫ ሲካሄድ ፌስቡክ ለሳምንታት ያህል ፓለቲካዊ መልዕክቶችን ቀንሶ ነበር። አሁን ይህንን አሠራር በሌሎች አገራትም እንደሚተገብር ተገልጿል።
የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ "ሰዎች ፓለቲካና ግጭት መመልከት አይፈልጉም" ሲል ተናግሯል።
ማኅበራዊ በሚለው ዝርዝር ውስጥ ምን አይነት ቡድኖች እንደሚካተቱ በተያያዥም በተለያየ ጉዳዮች ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ የሚያደርጉ ቡድኖች ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ አልተደገረም።
ለበርካታ ወራት ያህል ፌስቡክ በገጹ ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን በአግባቡ አይቆጣጠርም በሚል ተተችቷል።
ማርክ ዙከርበርግ እንደሚለውም፤ ሰዎች ፌስቡክ ላይ የሚቀላቀሏቸው ቡድኖች "ጤናማና ቀና" እንዲሆኑ ይፈለጋል።
"ከፖሊሲያችን ጋር ባይጻረሩም ሰዎች እንዳይገቡ የምንፈልጋቸው ቡድኖች አሉ" ብሏል።
ማኅበራዊ እንዲሁም ፓለቲካዊ ቡድኖችን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲቀላቀሉ የሚላኩ ማስታወቂያዎችን ረዘም ላለ ጊዜ እንዳገዱም ገልጿል።
"ውጥረትን ለማርገብና በማኅበረሰቡ ዘንድ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ውይይት እንዲኖር የጀመርነው ሥራ አንድ አካል ነው" ሲል መስራቹ ተናግሯል።
ፌስቡክ ላይ የሚገኙ ቡድኖች በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውሉት ማኅበራዊ ንቃት ለመፍጠርና የተለያዩ ንቅናቄዎችን ለማካሄድ ነው።
ፌስቡክ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ቢፈልግም በርካታ ተጠቃሚዎቹ የፓለቲካ ገጾችን እንደማይፈልጉ እንዳስታወቁ ገልጿል።
ፌስቡክ እአአ 2020 ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቡድኖችን ሰርዟል።
ለአንድ አላማ የተከፈቱ ገጾች በሌላ አካል የሚጠለፉበት አጋጣሚ አለ። እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው በዩናይትድ ኪንግደም 2019 ላይ በተካሄደው ምርጫ ወቅት የተከሰተው ነው።
ስለተለያዩ ከተሞች ጉዳዮች ውይይት ለማካሄድ ተከፍተው ወደ ጸብ ያመሩ የፌስቡክ ቡድኖች ነበሩ።
ጋርዲያን እንደዘገበው 40 ሺህ አባላት ያሉትና ለመሬት ሽያጭ የተከፈተን ቡድን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞችን በሚቃወሙ ሰዎች ወስደውታል።












