ባንክ 'ሃክ' አደረጉ የተባሉት ኬንያውያኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው

የ21 ዓመቷ አን ዋንቡኢ እና የ23 ዓመቱ አንቶኒ ሙዋንጊ ክሱን ተቃውመዋል።

የፎቶው ባለመብት, The Informer

የምስሉ መግለጫ, የ21 ዓመቷ አን ዋንቡኢ እና የ23 ዓመቱ አንቶኒ ሙዋንጊ ክሱን ተቃውመዋል።

ባንክ 'ሃክ' አድርገዋል የተባሉ ሁለት ኬንያውያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሰረተባቸው።

የጆሞ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ተማሪ የሆኑት ሁለቱ ወጣቶች ኤን ሲ ቢኤ ከተባለው ባንክ 220ሺህ የአሜሪካ ዶላር (24 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ) መስረቃቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ገንዘቡ ከባንኩ የተሰረቀው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

የ23 ዓመቱ አንቶኒ ሙዋንጊ እና የ21 ዓመቷ አን ዋንቡኢ ክሱን ተቃውመዋል።

ፖሊስ ግን ተማሪዎቹ ተጨማሪ 190 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ለመስረቅ በዝግጅት ላይ ነበሩ ብሏል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ በበኩላቸው ተማሪዎቹ የተከሰሱበትን ወንጀል አለመፈጸማቸውን እና እንዲያውም ባንኩ መሰል ጥቃት እንዳይሰርስበት ማስጠንቀቂያ ስለሰጡ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሲሉ ተከራክራዋል።

ጠበቃው እንደሚሉት አንደኛው ተከሳሽ አንቶኒ ሙዋንጊ የባንኩ የስልክ መተግበሪያ ላይ ያስተዋለውን የደህንነት ክፍተት ለባንኩ በትዊተር አማካኝነት በይፋ አሳውቆ ነበር።

ከባንኩ ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር አጭር የጸሑፍ መልዕክት በድጋሜ ልኳል።

ባንኩም አንቶኒ መሠስሪያ ቤታቸው ድረስ እንዲመጣ ካደረገ በኋላ በቁጥጥር ሥር እንዲውል አድርጓል ሲሉ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤት ለሕዳር 1/2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።