ፉኩሺማ፡ ጃፓን የኒውክሊየር ማብለያ ውስጥ የነበረ ውሃ ወደ ባህር ልታስገባ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጃፓን የፉኩሺማ ኒውክሊየር ማብለያ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለና በጨረር የተበከለ ውሃ ወደ ባህር መልሳ ልትከት እንደሆነ እየተዘገበ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2011 ዝናብ በቀላቀለ ከባድ አውሎንፋስ ማብለያው ሲጠቃ ለማቀዝቀዝ ጥቀም ላይ የዋለውም ው ወደ ባህር እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን የውሀው አወጋገድ ጉዳይ ለዓመታት ክርክር ሲካሄድበት የነበረ ነው።
ምንም እንኳን የአካባቢ ተቆርቋሪዎችና የአሳ አስጋሪወች ማህበራት በኒውክሊየር ማብለያው ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ውሃ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ነው ቢሉም ተመራማሪዎች ግን እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት አያስከትልም እያሉ ነው።
የጃፓን መንግሥት ደግሞ በጉዳዩ ላይ እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ አለመተላለፉን አስታውቋል።
ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆነው ውሃ ወደ ባህር የመለቀቅ ሂደት የሚጀምረው በአውሮፓውያኑ 2022 ሊሆን እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን ከመለቀቁ በፊት ግን የማጣራት ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ውሀውን ሙሉ በሙሉ ወደ ባህር የማስገባቱ ሂደት እስከ 30 ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን ውሃው የተበከለ አለመሆኑን ለማረጋገጥም ከተለያዩ ኬሚካሎችና ንጹህ ውሀ ጋር ይቀላለቀላል።
የጃፓኑ ኪዮዶ የዜና ወኪል እንደዘገበው ደግሞ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ውሳኔ እስከ ያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚወሰን ዘግቧል።
ጃፓን እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ዝም ብሎ መቀመጡ ለሌላ ጉዳዮች ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልን ቦታ እንደተሻማባት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር።
የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሂሮሺ ጃኪያማ እንዳሉት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም አይነት ውሳኔ ያልተወሰነ ሲሆን መንግሥት ግን በቅርቡ አፋጣኛም ውሳኔ ያስተላልፋል ብለዋል።
''ውሀውን የማስወገድ ስራውን ላለማጓተት ሲባል ፈጣን የሆነ ውሳኔ ማስተለለፍ አለብን'' ብለዋል ሚኒስትሩ ለጋዜጠⶉች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።
በርካታ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ውሀው ወደ ባህር እንዲገባ መደረጉ የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የአሳ አስጋሪዎች ማህበራት ደግሞ ውሳኔውን በመቃወም የተከከራከሩ ሲሆን ደንበኞቻቸው ውሀው ከተለቀቀበት አካባቢ የሚመጣ አሳን እንደማይገዟቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ተመራማሪዎች ውሃው እጅግ ሰፊ ቦታን በሚሸፍነው ፓሲፊክ ውቂያኖስ ውስጥ ሲገባ ከተፈጥሮአዊ ውሃው ጋር ስለሚቀላቀል እምብዛም ጉዳት አያስከትልም እያሉ ነው።












