ቴክኖሎጂ፡ የውጊያ ውሾችን ከርቀት መቆጣጠር የሚያስችል መሣሪያ ተሠራ

የፎቶው ባለመብት, Command Sight / US Army
የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ለውጊያ ውሾች ከርቀት ትዕዛዝ ማስተላለፍ የሚያስችል መሣሪያ ሠራ።
መሣሪያው እንደ መነጽር ያለ ሲሆን፤ በአንድ አካባቢ ያሉ ቁሳቁሶች ወይም ሰዎች አጠገባችን እንዳሉ አስመስሎ የሚያሳይ (ኦግመንትድ ሪያሊቲ) ነው።
መሣሪያው የተሠራው ኮማንድ ሳይት በተባለ ተቋም ሲሆን፤ ጥናቱ የሚመራው በአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ነው።
ውሾቹ ፈንጂና ሌሎችም መሰናክሎችን ከርቀት መለየት የሚችሉ ሲሆን፤ አዲስ የተሠራላቸው መነጽር ባለቤቶቻቸው ሩቅ ሆነው ትዕዛዝ እንዲሰጧቸው ይረዳል።
ውሾቹ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከላል።
ወታደሮች ለእንስሳት ትዕዛዝ የሚሰጡት በእጅ በመጠቆም ነበር። ይህን ለማድረግ ደግሞ ወታደሮቹ እና እንስሳቱ መጠጋጋት ይጠበቅባቸዋል።
መሣሪያው ተግባር ላይ ከዋለ ግን በርቀት ሆኖም እንስሳትን ማዘዝ ይቻላል።
ውሾቹ መነጽሩን ሲያደርጉ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚመራቸው ምስል ያያሉ። ወደየት መሄድ እንዳለባቸው ማሰልጠንም ይቻላል።
የውሾቹ ባለቤቶች ውሾቻቸው ምን እየተመለከቱ እንደሆነ ማየት ይችላሉ።
የወታደራዊ ኃይል ጥናት ክፍል ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ስቴፈን ሊ "በኦግመንትድ ሪያሊቲ (ኤአር) ውሾችን ማዘዝ ይቻላል። ቴክኖሎጂው ውጤታማ እንደሚሆን በጉጉት እየጠበቀ ነው" ይላል።
መነጽሮቹ ለእያንዳንዱ ውሻ እንዲሆኑ ነው የተዘጋጁት። መነጽሩን ሲያደርጉ ወደየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸው የሚጠቁም መረጃ ያገኛሉ።
በእርግጥ ከዚህ ቀደምም ውሾችን ከአደጋ ለመከላከል መነጽር ይደረግላቸው ነበር። አዲሱ መሣሪያ ግን ኤአር የተገጠመለት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
መሣሪያውን ያዘጋጀው ተቋም መስራች ዶ/ር ኤጄ ፔፐር፤ ቴክኖሎጂው ገና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ቢሆንም ውጤቱ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
መስራቹ ማትር በተባለ ውሻው ላይ ብዙ ሙከራ አድርጓል።
አርዩኤስአይ በተባለ ተቋም ምርምር የሚሠራው ጀስቲን ብሮንክ፤ መሣሪያው "አላስፈላጊ ወጪ ቢመስልም በጣም ጠቃሚ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ውሾችን በኤአር ከርቀት መቆጣጠር መቻል ከታክቲክ አንጻር ጥቅም ያስገኛል" ብሏል።












