ኮሮናቫይረስ፡ 4 ሚሊዮን ሩዋንዳውያንን ለማስተማር የወጠነው የሬዲዮ ድራማ

የ14ና የ20 ዓመት ወጣቶች በድራማው ላይ ሲተውኑ

የፎቶው ባለመብት, WATERAID/ELENA HEATHERWICK

በሩዋንዳ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው የሬዲዮ ድራማ እየጻፉ እና እያዘጋጁ ነው። ድራማው የኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ መልዕክቶች ተካተውበታል ተብሏል።

የሬዲዮ ድራማው የሚዘጋጀው ከወተር ኤይድ ጋር በመተባበር ነው። ድራማው በኢሺንጊሮ ሬዲዮ የሚተላለፍ ሲሆን 4 ሚሊዮን አድማጮችን ለመድረስ ማሰባቸውን ይናገራሉ።

ይህም ማለት የሩዋንዳ ሕዝብ 1/3ኛ ማለት ነው ተብሏል።

ሩዋንዳ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከሶስት ሳምንት በፊት የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ የመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ማርታ ኡዊማና በሩዋንዳ የወተርኤይድ ቢሮ በትምህርት ቤቶች የሚካሄደው የውሃና ንጽህና አጠባበቅ ፕሮግራም ኦፊሰር ስትሆን " ድራማው ኮቪድ-19 በመከላከል ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል" ትላለች።

ድራማው ሰዎች በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ መሰረት ለ14 ቀን ቤታቸው እንዲቀመጡ ያበረታታል የምትለው ማርታ " ሬዲዮ ሕዝቡን ለመለወጥ አቅም አለው" ስትል የድራማውን አስፈላጊነት ትገልጻለች።።

አፍሪካውያን በአገራቸው ባለው ደካማ የጤና ስርዓትና የንፁህ ውሃ አቅርቦት እጥረት የተነሳ በቫይረሱ ክፉኛ ሊጎዱ ይችላሉ ተብሎ ይሰጋል።

የድረማው ደራሲያንና ተዋንያን

የፎቶው ባለመብት, WATERAID/ELENA HEATHERWICK

ከአራት ሩዋንዳውያን መካከል አንዱ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሲሆን ቴሌቪዥንም የማግኘት እድሉ አናሳ ነው። በዚህ ሁኔታ ሬዲዮ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል።

በድራማው ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ድራማውን ከመድረስ፣ ከማዘጋጀት፣ አርትኦት ከመስራትና ግብዓተ ድምጽ እስከመሰብሰብ ድረስ ራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው መስራታቸውን ይናገራሉ።

በድራማው ላይ የምትተውነዋ ሶላንጅ " እናቴን እንዴት እጇን መታጠብና ራሷን በቫይረሱ እንዳትያዝ መከላከል እንደምትችል አስተማርኳት" በማለት ድራማው በማህበረሰቡ ህይወት ውስጥ እያመጣ ያለውን ለውጥ ትናገራለች።

ይህም በድራማው ላይ በመሳተፏ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቧን ወሳኝ የጤና ትምህርት በማስተማሯ ኩራትና ደስታ እንዲሰማት አድርጓል።

እናቷም፣ ኤሜልዜ ሙካሺያካ " ጎረቤቶቼ ሁሉ ድራማውን ያደምጣሉ፤ ስለእርሷም[ስለልጃቸው] ሲያወሩ ለጉድ ነው ፤ያ ደግሞ እንድኮራ አድርጎኛል" ብለዋል።

አክለውም " ንጽህና ቤት ከሄድኩ በኋላ እጄን አልታጠብም ጉድጓዱንም አልከድንም ነበር። አሁን ጥሩ የንጽህና አጠባበቅ ምን ማለት እንደሆነ እና የመልካም ጤና ምንጭ መሆኑንም ተረድቻለሁ" ብለዋል።

ኮሮና
Banner