ኮሮናቫይረስ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ትናንት አርብ አመሻሽ ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ በጽህፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተወው ነበር። በዚህ መግለጫቸው ላይም የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የጤና እና የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ተቋቁሞ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ሲከታተል መቆየቱን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት አዳዲስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተወስኗል በማለት ውሳኔዎቹን ገልፀዋል።.
- ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ይወሰዳል
ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ለ14 ቀናት በራሱ ወጪ ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስታውቀዋል።
- በረራ ይደረግባቸው የነበሩ ከ30 በላይ አገራት በረራ እንዲቋረጥ ተደርጓል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከ 30 በላይ አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ መወሰኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አየር መንገዱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቀዋል።
"አየር መንገዱ 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል። በዚህም ወደፊት ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል" ብለዋል።
- የእምነት ተቋማት
የአምልኮ ስርዓቱ እና ልምዱ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም "በእነሱ [ኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች] በኩል መልዕክት እንደሚተላለፍ ይጠበቃል" ያሉ ሲሆን፤ የፕሮቴስታንት መሪዎችም ቴክኖሎጂን በመታገዝ አገልግሎት እንዲሰጡ አማራጭ መቀመጡን ተናግረዋል።

በእስልምናም የሚደረጉ ሰላቶች ንክኪ ስለሚኖራቸው፤ የሃይማኖት መሪዎች እርምጃ እንደሚወስዱ እና መግለጫ እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል ብለዋል።
- በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች
በማረሚያ ቤቶች በሽታው ከገባ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ታራሚዎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች ወስዶ ዘርዘር ለማድረግ ተጨማሪ ቦታዎች ተዘጋጅቷል ብለዋል።
አክለውም አዳዲስ ታራሚዎች ምርመራ ሳይደረግላቸው ወደ ማረሚያ ቤት አይገቡም ብለዋል። እንዲሁም የቤተሰብ ጥየቃ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም መደረጉን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ ህጻናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰ እና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው እንዲለቀቁ መወሰኑን ተናግረዋል።
- በውጪ አገር ዜጎች ላይ ስለደረሰው ጥቃት
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከሰሞኑ የወረርሽኙን ስርጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ በውጪ አገር ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት ''ኢትዮጵያዊ ባህሪ የሌለው ነው'' በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል።
- የበጎ አድራጎት ሥራዎች
ከሰሞኑ በርካታ ወጣቶች ሰዎችን እጅ ማስታጠብ ጨምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ነበር። መንግሥት የበጎ አድራጎት ሥራዎቹን በአክብሮት የሚመለከተው ነው ካሉ በኋላ፤ ነገር ግን አገልግሎቱን የሚሰጡ ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል።
- የሕክምና ባለሙያዎች ጥረት
ጠቅላይ ሚንስትሩ የእስካሁኑን የሕክምና ባለሙያዎችን ጥረት አድንቀዋል። የቫይረሱ ስርጭት የሚስፋፋ ከሆነም በሽታውን ለማሸነፍ ብዙ ጥረት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
- ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚገኙ ድጋፎች
ከጃክ ማ፣ ከቢል ጊቴስ እና ከዓለም ባንክ በተገኙ ድጋፎች የዜጎች ሕይወት እንዳያልፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
- የምሽት መዝናኛ ቤቶች ይዘጋሉ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመሽት መዝናኛ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ይሆናሉ ብለዋል። በጠባብ ቦታ ላይ በርካታ ሰዎች ስለሚያስተናግዱ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ዝግ ይደረጋሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
"በሽታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራችንን እስክናረጋግጥ ድረስ የምሽት መዝናኛዎች እንዲዘጉ ተወስኗል" ብለዋል።
- ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች
ጠቅላይ ሚንስትሩ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት በሞከሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው አሁንም ሕጋዊ የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ ይቀጥላል ብለዋል።
- ለክልሎች የሚደረገው ድጋፍ
በክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ምረመራ የማድረግ አቅማቸውን ለማሳደግ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበረ አስታወሰዋል። ለዚህም የሚረዳ የምረመራ እና የማዳን ሥራ እንዲሰራ ተግባብተናል ብለዋል።
- ምርጫ
ወረርሽኙ ከወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ስለሚኖረው ጫና ሲያስረዱ፤ "ምርጫ ቦርድ የራሱን ግምገማ እያካሄደ ነው፤ ግምገማውን መሰረት በማድረግ የመጨረሻው ውጤት ይፋ ይደረጋል" ብለዋል።
- የመጠጥ ውሃ እጥረት
የመጠጥ ውሃ እጥረት ባለባቸው ቦታዎች በቦቴ የማቅረብ ሠራዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። በተለይ በከተማ አከባቢ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩን አንስተዋል።
- "ይቅርታ"
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው መጨረሻ ላይ "የብልጽግና ፓርቲ የገንዘብ መዋጮ ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን እና የፖለቲካ ምሁሮችን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር በርካቶች ማዘናቸውን ሰምቻለሁ" ብለዋል።
"ጉዳዩ የማይመለከታችሁ እና በንግግሬ እንድትከፉ የሆናችሁ፣ የተማራችሁ እና በተማራችሁበት ዘርፍ አገራችሁን በቅንነት የምታገለግሉ፣ ውጤትም ያመጣችሁ ሰዎች ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት ቢሆንም፤ ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት መሆኑን በግልጽ ባለማስቀመጤ እናንተን ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።















