ዱባይ ኤክስፖ 2020፡ በኮሮናቫይረስ የዘገየው ትልቁ ዓለም አቀፍ ትዕይንተ ሕዝብ ተከፈተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤክስፖ 2020 በደመቀ ሥነ ሥርዓት ሐሙስ ምሽት ተከፍቷል

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የዘገየው ዱባይ ኤክስፖ 2020 በዱባይ የተከፈተ ሲሆን አዘጋጆቹ ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ከመላው ዓለም በርካታ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ለማድረግ አልመዋል።

ከ190 በላይ አገራት የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች በ438 ሔክታር ቦታ ላይ ባህሎቻቸውን እና ፈጠራዎቻቸውን እያሳዩ ናቸው።

የዱባይ መንግሥት ለዝግጅቱ በግምት ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል።

ዝግጅቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 25 ሚሊዮን ጎብኝዎችን በመሳብ በኤሚሬትስ ቱሪዝምን እና ኢንቨስትመንትን እንደሚያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል።

አዘጋጆች በትኬት ሽያጩ "ተደስተናል" ቢሉም ተንታኞች ግን በዓለም አቀፍ ጉዞ ላይ ገደቦች በመኖራቸው ዕቅዱን ስለማሳካቱ ጥርጣሬ አለን ብለዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት ከጸደቁ የኮቪድ-19 ክትባቶች አንዱን ሙሉ ለሙሉ የተከተቡ የሁሉም አገር ዜጎች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን መጎብኘት ይችላሉ።

ወደ ኤግዚቢሽኑ ለመግባት፣ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሁሉ የክትባት ማረጋገጫ ወይም ቫይረሱ እንደሌለባቸው የሚያሳይ የፒሲአር ምርመራ ውጤት እንዲያሳዩ ይጠየቃሉ። ቲኬት ለያዙ ሰዎች በቦታው ነጻ ምርመራም ይኖራል።

የዱባይ ገዥ ሼክ ሙሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ሐሙስ ምሽት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ዝነኞችን ባካተተ ሥነ ሥርዓት ኤክስፖው መከፈቱን አስታውቀዋል።

ከዝነኞቹ መካከል ጣሊያናዊው አንድሪያ ቦሴሊ፣ የእንግሊዙ የፖፕስታር ኤሊ ጎልዲንግ እና ቻይናዊው ፒያኖ ተጫዋች ላንግ ላንግን ይገኙበታል።

ሼክ መሐመድ በዚህ ሳምንት ለአል ባያን ጋዜጣ ስለ ሁነቱ ሲናገሩ "በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ የተቀረጸ ልዩ ክስተት" ይሆናል ሲሉ ገለጸዋል።

"የሰው ልጅ በሚያስፈልገው ዓለም አቀፍ ትብብር መሠረት በዚህ ኤክስፖ ላይ ኢንቨስት ስናደርግ የ192 አገሮች ተወካዮችን ወደ መቻቻል ምድር በመቀበላችን ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሼክ መሐመድ ስለሁነቱ "በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ የተቀረጸ ልዩ ክስተት" ይሆናል ሲሉ ገለጸዋል

የቻይና ቤት በኤግዚቢሽኑ ላይ ካሉት ግዙፍ ትዕይንቶች አንዱ ሲሆን የባህላዊ ፋኖስ ቅርጽ አለው። የሞሮኮ ደግሞ በባህላዊ የጭቃ ግንባታ ዘዴ የተሠራ ነው።

የእንግሊዝ ቤት ከሟቹ የሳይንስ ሊቅ ስቴፈን ሃውኪንግ ፕሮጀክት የመነጨ ሲሆን 21 ሜትር ቁመት ያለው መዋቅር ሲኖረው ከአልጎሪዝም የተገኙ "አስገራሚ የዕድገት መልዕክት" የሚሉ ቃላት ሰፍረውበታል።

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ምክንያት በዝግጅቱ ላይ አንዳንዶች ትችቶች ሰንዝረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል አገራት በኤክስፖው እንዳይሳተፉ እና ኩባንያዎች ስፖንሰርነታቸውን እንዲያቆሙ አሳስቧል።

"በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፖለቲካ እና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ በሚናገሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ጠበቆች እና መምህራን ላይ ስልታዊ ክስ" እና የአገሪቱን 80 በመቶ ሕዝብ በሚይዙት "የውጭ አገር ሠራተኞች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች" እንደሚካሄዱ አንድ መረጃ ጠቅሷል።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበውን ውንጀላ "ትክክል አይደለም" በማለት ውሳኔውን ውድቅ አድርጓል።

የአገሪቱ ሕጎች ለሁሉም ዜጎች እና ነዋሪዎች ፍትሃዊ አያያዝ እንዲኖር ይደነግጋል ሲልም አክሏል።