ትራምፕ፡ ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ጠንከር ያለ ንግግር” ጀምራለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ጠንከር ያለ ንግግር ጀምራለች” አሉ።
የአሜሪካ ጦር በባሕር ሰላጤው አካባቢው ያለውን ይዞታ ማጠናከሩን ተከትሎ ኢራን ከዩኤስ ጋር ምክክር መጀመሯን ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተካረረ የመጣ ሲሆን ትራምፕ ውይይት “ተቀባይነት” ያለው ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢራን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን የሆኑት አሊ ላሪጃኒ ድርድር ለማድረግ የሚደረገው ማዕቀፍ ሒደት ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኢራን ኒውክሌር ለማብላላት የምታደርገውን ጥረት ተከትሎ ጣልቃ እንደሚገቡ ሲዝቱ የቆዩት ትራምፕ በቅርቡ የተካሄደውን ሕዝባዊ አመፅ አስታከው ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ተናግረዋል።
ቴህራን በበኩሏ በየብስም ሆነ በምድር ለሚሰነዘር ጥቃት “አፀፋዊ እና ከባድ ምላሽ” እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች።
ኢራን ለዓለም ንግድ ወሳኝ በሚባለው እና የመርከቦች መተላለፊያ በሆነው ሆርሙዝ ሰርጥ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርግ ይጠበቃል።
ኢራን የአሜሪካ ኃይሎች ባሉበት አካባቢ የትኛውንም ዓይነት “ደኅንነቱ ያልተጠበቀ እና ፕሮፌሽናል ያልሆነ ባሕሪ” እንዳታሳይ ዩኤስ አስጠንቅቃለች።
አሜሪካ ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን የተሰኘው ግዙፍ የጦር መርከብን ጨምሮ በርካታ የጦር ኃይሎቿን ወደ ባሕረ ሰላጤው አሰማርታለች።
ቅዳሜ ዕለት ሁለት ፍንዳታዎች መሰማታቸው በሀገሪቱ ውጥረት እንዲነዛ አድርጓል። የኢራን መንግሥት ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት በጋዝ ምክንያት ነው ብሏል።



















