አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት፡ ዋና ዋና እውነታዎች በካርታ
የፎቶው ባለመብት, Airbus
አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሲገደሉ፤ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ ጥቃት መፈጸም ቀጥላለች።
የእስራኤል መከላከያ እንዳለው፤ ከአሜሪካ ጋር በሚወስደው ጥምር ጥቃት በማዕከላዊ እና ምዕራባዊ ኢራን የሚገኙ የአየር መቃወሚያዎች ዒላማ ተደርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የዋሽንግተን ግብ እስከሚሳካ ድረስ "በሙሉ ኃይል ዘመቻው ይቀጥላል" ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ የሚፈጽመው ጥቃት ያነጣጠረው የቴህራን ከፍተኛ የፖለቲካ እና ደኅንነት ባለሥልጣናት የሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች ላይ እንደሆነ ገልጿል።
ከኢራን መዲና ቴህራን የወጡ እና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ ምሥሎች ቅዳሜ ዕለት ከሕንጻዎች አናት ላይ ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።
የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' በዕለቱ የተነሱ የሳተላይት ምሥሎችን ተመልክቷል።
ምሥሎቹ ከኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ አናት ላይ ጭስ ሲወጣም ያሳያሉ።
በቴህራን እና 12 ሌሎች ከተሞች የሚገኙ ጥቃት የተፈጸመባቸው 13 ሥፍራዎችን ቢቢሲ ቬሪፋይ ማረጋገጥ ችሏል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 700 ሰዎች ተገድለዋል። አምስት የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አባላት ሲሞቱ አራት ደግሞ ተጎድተዋል።
በኢራን ደቡባዊ ክፍል ሚናብ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ ቅዳሜ ዕለት የሚሳዔል ጥቃት ደርሶ ቢያንስ 153 ሰዎች መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ቢቢሲ ይሄንን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
የኢራን የባሕር ኃይል መቀመጫ የሆኑት በደቡባዊ የአገሪቱ ግዛት ኮናራክ የሚገኙት ኬራማንሻህ እና ታብሪዝ ዒላማ ተደርገዋል።
ትራምፕ እንዳሉት፤ ዘጠኝ የጦር መርከቦች ወደ ኢራን ዘልቀው እንዲገቡ ተደርጎ የአገሪቱን የባሕር ኃይል ዋና መቀጫ "ክፉኛ መጉዳት" ተችሏል።
የእስራኤል ጥቃት በሊባኖስ
እስራኤል በሊባኖስ፣ ቤይሩት ሄዝቦላህ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሰኞ ዕለት ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ሄዝቦላህ የእስራኤሏ ሀይፋ ከተማ ላይ ሮኬቶች ከተኮሰ በኋላ እስራኤል የአጸፋ ጥቃት ፈጽማለች።
እሑድ ዕለት ከኢራን በተተኮሰ ሚሳዔል ምክንያት እስራኤል ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።
እስራኤል በሊባኖስ የፈጸመችው ጥቃት የሔዝቦላህ ዋና መቀመጫ የሆነው ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ በመዲናዋ ቤይሩት እና ለከተማው አውሮፕላን ማረፊያ በቀረብ አካባቢዎችም ጥቃት ተሰንዝሯል።
ኢራን ጥቃት የፈጸመችው የት ነው?
ኢራን የአጸፋ እርምጃ የወሰደቸው በባሕረ ሰላጤው አገራት በሚገኙ የአሜሪካ እና እስራኤል የጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው እና ወዳጅ በሆኑ አገራት ላይ ነው።
በኳታር የነዳጅ ማምረቻ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ከዚያም የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የኢራንን ሁለት ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ ሰባት ሚሳዔሎች እና አምስት ድሮኖች ማክሸፉን አስታውቋል።
የእስራኤሏ ቤት ሻሜሽ ላይ እሑድ ዕለት በተፈጸመ የሚሳዔል ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላይ በደረሰው ጥቃት የቱሪስት መዳረሻ በሆኑት ዱባይ እና አቡ ዳቢን ጨምሮ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ብዙዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
የኩዌት የጤና ሚኒስቴር እንዳለው እሑድ አንድ ሰው ተገድሏል። አሊ አል-ሳሌም የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በርካታ ሚሳዔል ቢተኮስም ማምከን እንደተቻለ ተገልጿል።
የኩዌት መከላከያ ኃይል "በስህተት" ሦስት የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች ላይ ተኩሶ መከስከሳቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።
በተዋጊ አውሮፕላኖቹ ውስጥ የነበሩ ስድስት ሠራተኞች እንዳልተጎዱ ተገልጿል።
ሰኞ ዕለት በኢራቅ እና አሜሪካ ጥምረት በኤሪልቢ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ሦስት ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸው ተገልጿል።
የባህሬን ብሔራዊ ኮምዩንኬሽን እንዳለው፤ ቅዳሜ ዕለት በአሜሪካ ባሕር ኃይል መቀመጫ ላይ ሚሳዔል ተተኩሷል።
ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ እና ከመኪና ላይ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሚሳዔል ሲወድቅ እና ፍንዳታ ሲከተል ያሳያል። በአካባቢው ስብርባሪዎች አየር ላይ ሲበተኑም ይታያል።
እሑድ ምሽት ላይ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ሰፈር የደረሰ የድሮን ጥቃት እሳት ቢያስነሳም ሰዎች እንዳልተጎዱ አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል። በባህሬን ላይ ኢራን ባደረሰችው ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን አክለዋል።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ንብረት የሆነው ነዳጅ አምራች አራማኮ የሚያስተዳድረው ራስ ታናውራ ነዳጅ ማጣሪያ ሰኞ ዕለት በሁለት ድሮን ጥቃት እንደደረሰበት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በዮርዳኖስ ላይ የተተኮሰ ባለስቲክ ሚሳዔልን ማክሸፍ እንደተቻለ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የኦማን ብሔራዊ ጣቢያ እንዳለው እሑድ ዕለት በዱቃም የንግድ ወደብ ላይ ሁለት ድሮኖች ተተኩሰው አንድ ሠራተኛ ተጎድቷል።
በቆጵሮስ ጥቃት የተፈጸመው የት ነው?
የቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዶሊዲስ እንዳሉት፤ እሑድ እኩለ ሌሊት ላይ የኢራን ድሮኖች የብሪታኒያ አየር ኃይል ሰፈርን መትተዋል።
የተጎዱ ሰዎች እንደሌሉ እና የአየር ኃይል መቀመጫውም "ውስን ጉዳት ብቻ" እንደደረሰበት ተገልጿል። የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች እና ቤተሰቦቻቸው አካባቢውን ለቅለው እንዲወጡ ተደርጓል።
ሰኞ ዕለት የቆጵሮስ መንግሥት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ሁለት ተጨማሪ ድሮኖች ወደ አየር ኃይሉ ቢተኮሱም ማክሸፍ ተችሏል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ምን ጫና አሳደረ?
ሰኞ ዕለት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል። የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት እና በመካከለኛው ምሥራቅ የቀጠለው ጦርነት ነዳጅ አምራቾች እና አጓጓዠችን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቷል።
የዓለም ትልቁ የተጣራ ነዳጅ አምራች ኳታር ኢነርጂ በደረሰበት ጥቃት ሥራ በማቋረጡ ምክንያት የአውሮፓ የነዳጅ ዋጋ ከ30 በመቶ በላይ ጨምሯል።
ኳታር ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛውን ትሸፍናለች። በሆርሙዝ ሰርጥ ባለፉት ቀናት ጥቃቶች ቀጥለዋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም