ዩኬ፤ ሱዳንን ጨምሮ ከአራት አገራት ለሚሄዱ ተማሪዎች የምትሰጠውን ቪዛ አቋረጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም ከአራት አገራት ለሚሄዱ ዜጎች የተማሪዎች ቪዛ መስጠት ማቋረጧን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻቢና መሐሙድ አስታወቁ።

ለአንድ ወር ያህል ቪዛ የማይሰጣቸው አገራት አፍጋኒስታን፣ ካሜሩን፣ ምያንማር እና ሱዳን ናቸው። አገራቱ ዕገዳ የተጣለባቸው "የቪዛ ሥርዓቱን በዝብዘዋል" በሚል ነው።

ዩኬ ለአፍጋኒስታን የሠራተኞች ቪዛ መስጠትም እንዳቋረጠች ተገልጿል። የአራቱ አገራት ዜጎች የተማሪ ቪዛ ካገኙ በኋላ በዩኬ ጥገኝነት በመጠየቅ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ "እርዳታችንን የሚፈልጉ ሰዎችን በአግባቡ ማገዝ እንድንችል ዕገዳውን መጣል አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2021 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ በተማሪ ቪዛ ዩኬ ገብተው ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል። በዩኬ ጥገኝነት ከሚጠይቁ ሰዎች የተማሪ ቪዛ ያላቸው 13% ይሆናሉ።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻቢና "ደግነታችንን እየበዘበዙ ላሉ አገራት ቪዛ ከልክለናል። ሕጋዊ ሥርዓትን በማስጠበቅ ድንበራችንን እናስከብራለን" ሲሉ አስረድተዋል።

የተማሪ ቪዛ ዕገዳ ከተጣለባቸው አራት አገራት ወደ ዩኬ የተጓዙ እና መንግሥት እየደገፋቸው የሚገኙ ሰዎች 16,000 መድረሳቸው ተመልክቷል።

ከ2021 ወዲህ የተማሪ ቪዛ ካገኙ አፍጋኒስታናውያን መካከል 95% ጥገኝነት ጠይቀዋል። ካሜሩናውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ስድስት እጥፍ ሲጨምሩ ሱዳናውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በ330% አድጓል።

የሠራተኛ ቪዛ ያላቸው አፍጋኒስታናውያን ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በዩኬ እንደሚቆዩም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ከወግ አጥባቂ ፓርቲዎች እየደረሰባቸው ባለው ጫና ምክንያት ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ጥብቅ ፖሊሲዎች እየተገበሩ ነው።

በጀልባ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል ለጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ የሚሰጥበት ጊዜ ወደ 30 ወራት ብቻ መቀነሱ ባለፈው ሳምንት ይፋ ተደርጓል።

ከወራት በፊት ደግሞ የአንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ መንግሥታት የየአገራቸውን ስደተኞች መልሰው የማይቀበሉ ከሆነ የቪዛ ክልከላ እንደሚጣል ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው፤ ዩኬ ስደተኞችን በብዛት በማስተናገድ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።