በዩክሬን እና ሩሲያ የመጀመሪያው ቀን ድርድር "ትርጉም ያለው ለውጥ" መታየቱን አሜሪካ አስታወቀች
የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service of Ukraine/Anadolu via Getty Images
ሩሲያ እና ዩክሬን በጄኔቫ ያደረጉት የመጀመሪያ ቀን ድርድር ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል "ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን" የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ተናገሩ። ሁለቱ አገራት በዛሬው ዕለት የሁለተኛ ቀን ድርድራቸውን እንደሚቀጥሉም ተገልጿል።
ዊትኮፍ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁለቱንም ወገኖች ለድርድር በማቅረብ ረገድ ያገኙት ስኬት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል" ብለዋል። "በዚህ አስከፊ ግጭት ውስጥ የሚፈሰውን ደም ለማስቆም" የሚደረገው ጥረት ውስጥ በመሳተፋቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ጽፈዋል።
ከፍተኛ የዩክሬን ተደራዳሪ የሆኑት ሩስተም ኡሜሮቭ በበኩላቸው የመጀመሪያው ቀን ድርድር "በተግባራዊ ጉዳዮች" እና ስምምነት ሊደረስባቸው "በሚችሉ መፍትሄዎች የአተገባበር ሁኔታ" ላይ ያተኮረ እንደነበረ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ ገልጸዋል።
ይህ ከሆነ ከአጭር ጊዜ በኋላ በቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ አሜሪካ ለሩሲያ እና ዩክሬን ባቀረበችው ሐሳብ መሠረት አገራቸው ጥቃት ከመፈጸም ለመታቀብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
"እኛ ጦርነት አንፈልግም" ያሉት ዜሌንስኪ፤ ዩክሬናውያን እዚህ ጦርነት ውስጥ የገቡት "አገራቸውን እና ነጻነታቸውን ለመከላከል" መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።
"ጦርነቱን ለማቆም ወደሚችል ስምምነት በፍጥነት ለመሻገር ዝግጁ ነን። ጥያቄው መቅረብ ያለበት ለሩሲያውያን ብቻ ነው፤ የሚፈልጉት ምንድነው?" ሲሉም ጠይቀዋል።
የሩሲያው አርአይኤ የዜና ወኪል ምንጭ ጠቅሶ ባወጣ ዘገባ፤ ስድስት ሰዓት የቆየው የማክሰኞው ድርድር ውጥረት የበዛበት እንዲሁም የሁለትዮሽ እና የሦስትዮሽ ቅርጾችን ይዞ የተካሄደ እንደነበር አስረድቷል።
ሞስኮ በዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከከፈተኝ አራት ዓመት ሊደፍን አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚካሄደው ይህ ድርድር የሚመራው በልዩ መልዕክተኛው ዊትኮፍ እና በትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ነው።
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ረዳት የሆኑት ቭላድሚር ሜዲንስኪ ደግሞ ሩሲያን ወክለው የቀረቡ ዋና ተደራዳሪ ናቸው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የሦስትዮሽ ድርድሮችን አካሂደው የነበረ ሲሆን የአሁኑ ሦስተኛ ዙር ነው።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን ማግኘትን በተመለከተ ከያዘችው ጥግ የያዘ አካሄድ መለስ አለማለቷን ተከትሎ የአሁኑ ድርድር ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ አልተጣለበትም።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን በሰጡት አስተያየት፤ በስዊዘርላንድ የሚካሄደው ድርድር ፍሬ እንዲያስገኝ የማድረግ ድርሻ የዩክሬን እንደሆነ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ የሩሲያን ኃላፊነት በተመለከተ ግን ምንም ሳይጠቅሱ ቀርተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ ከሩሲያ ጋር ሲነጻጸር አገራቸው ብዙ ነገሮችን እንድትተው እየተጠየቀች መሆኑን በማንሳት ተችተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ሩሲያ ሰፊውን የምሥራቅ ዶንባስ ግዛት ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች። ሞስኮ ቀሪውም የግዛቱ ክፍሎች ተላልፈው እንዲሰጧት የምትፈልግ ቢሆንም ዩክሬንን ይህንን ሐሳብ በጽኑ ተቃውማለች።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም