የቀድሞው የጎግል ኃላፊ አሸባሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን 'ሊጠቀሙ ይችላሉ' ብለው እንደሚሰጉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የጎግል ስራ አስፈጻሚ ኤሪክ ሽሚት፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) በአሸባሪዎች ወይም "አደገኛ አገራት" "ንጹሃንን ለመጉዳት" ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገለጹ።

ኤሪክ ሽሚት፤ "እኔ የማነሳው ስጋት ብዙ ሰዎች የሚናገሩት አይደለም። እኔ የምናገረው ከፍተኛ ስለሆነ አደጋ ነው" ሲሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

እአአ ከ2001 እስከ 2017 ድረስ በጎግል ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የቆዩት የቴክ ቢሊዮነሩ፤ "ሰሜን ኮርያ ወይም ኢራን፣ ወይም ሩስያ ጭምር" ቴክኖሎጂውን በራሳቸው መንገድ ሊቀበሉት እና ባዮሎጂካል መሳርያ ለመፍጠር አላግባብ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አንስተዋል።

መንግሥታት፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሚያበለጽጉ የግል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ክትትል እንዲያደርጉም የጠየቁ ሲሆን ከልክ የሆነ ቁጥጥር ግን ፈጠራን ሊያደናቅፍ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ፤ የተሻሻለ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለማበልጸግ ጥቅም ላይ የሚውሉ ኃይለኛ ማይክሮቺፖች ወደ ሌሎች አገራት እንዳይላኩ የጣለችውን እገዳ እንደሚደግፉ የቀድሞው የጎግል ኃላፊ ገልጸዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያስተላለፉት ይህ እገዳ ከ18 አገራት በቀር ሌሎች ማይክሮቺፖቹን እንዳያገኙ የሚከለክል ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ውሳኔ ተፎካካሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎትን ላይ የሚያደርጉትን ምርመራ እንዲዘገይ ለማድረግ ያለመ ነው። ውሳኔ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ሊቀለበስ የሚችል ነው።

ኤሪክ ሽሚት፤ "ክፉ ጎል" አላቸው ያሏቸውን "ሰሜን ኮርያ፣ ኦራን እና ሩስያን" ጠቅሰው፤ "ይህ ቴክኖሎጂ ለእነርሱ ለመቀበል ፈጣን በመሆኑ አላግባብ ሊጠቀሙበት እና እውነተኛ ጉዳት ሊያደርሱበት ይችላሉ" ብለዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተሳሳተ ሰው እጅ ላይ ከወደቀ መሳሪያዎችን ለመፍጠር እና "አንዳንድ ክፉ ሰዎች መጥፎ ባዮሎጂካል ጥቃት" እንዲፈጽሙ ሊያደርግ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"እንደ ኦሳማ ቢን ላደን ስላሉ ሰዎች ሁሌም እሰጋለሁ። አንዳንድ እውነተኛ ክፉ ሰዎች ከዘመናዊው ህይወታችን አንዱን ክፍል ተቆጣጥረው ንጹሃንን ሊጎዱ እንደሚችሉ አስባለው" ሲሉም ተደምጠዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቀድሞው የጎግል ኃላፊ የሚያቀርቡት ምክረ ሀሳብ መንግሥት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ማበልጸግ ላይ ክትትል በማድረግ እና ዘርፉን ከልክ በላይ በመቆጣጠር መካከል አማካዩን መተግበር አለበት የሚል ነው።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በብዛት የሚበለጽገው በግል ኩባንያዎች እንደሆነ የሚናገሩት የቀድሞው የጎግል ኃላፊ፤ "መንግሥት የምንሰራውን ነገር መረዳቱ እና እኛ ላይ ክትትል ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

ኤሪክ ሽሚት ይህንን የተናገሩት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስብሰባ በተካሄደባት ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ሆነው ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የተመለከተ ዓለም አቀፍ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆኑም።

አሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ስምምነቱ "ገና በማኮብኮም ላይ ያለውን ለውጥ አምጪ ኢንዱስትሪ ሊገድል ይችላል" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የጎግል ቀድሞ ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፤ አውሮፓ ውስጥ ያለው ከልክ ያለፈ ቁጥጥር "ከኤሌክትሪክ መፈጠር ወዲህ በጣም አስፈላጊ አብዮት ሆኖ የመጣው የሰው ሰራሽ ልህቀት፤ በአውሮፓ እንዳይፈጠር አድርጓል" ብለዋል።

የኤሪክ ሽሚት "ቁጥጥር ይደረግ" የሚል አቋም የያዙት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ብቻ አይደለም። የቀድሞው የጎግል ኃላፊ፤ ህጻናት ትምህርት ቤት ውስጥ ስልክ መያዝ እንደሌለባቸው ከሚከራከሩ ሰዎች መካከል ናቸው።

ጎግል፤ በዓለም ላይ በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የ"አንድሮይድ" የሞባይል ኦፕሬቲንግ ስርዓት የገዛው ሽሚት የኩባንያው ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ነው። አሁን ደግሞ ህጻናት ስልክ እንዳይዙ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ይደግፋሉ።

ሁኔታዎች የቴክኖሎጂ ሰዎችን ዓለም 'በዚህ መልኩ ትሰራለች' ብለው በሚያስቡት ልክ ላለመሆናቸው ኃላፊነት እንደሚወስዱ የሚናገሩት ኤሪካ ሽሚት፤ የህጻናት ጉዳይ ግን በተለየ መልኩ እንደሚረብሻቸው አስረድተዋል።

"ስማርት ስልኮች ልጆች ጋር መድረሱ የማይጎዳ ነው። ክትትል ብቻ ያስፈልጋቸዋል። ልጆች በኦንላይን ዓለም ላይ ካለው መጥፎ ነገር መጠበቅ እንዳለባቸው ሁላችንም የምንስማማበት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የቀድሞው ኃላፊ፤ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ስልክ እንዲከለከሉ የሚደረጉ ቅስቀሳቸዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይደግፋሉ። "የዓለማችን አጅግ አስፈላጊ ሰዎች በሆኑት የቀጣዩ ትውልድ አባላት ላይ እንዲህ አይነቱን ትልቅ፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሙከራ ለምን እናከናውናለን?" ሲሉም ይጠይቃሉ።