በወንዶ ገነት 'ሴቶች ሱሪ መልበስ የለባቸውም' በሚል ፆታዊ ትንኮሳ ከመድረሱ ጋር በተያያዘ ስድስት ሰዎች መታሰራቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, በቪዲዮው ላይ ታዳጊዎች እና ጎረምሶች ከባጃጅ ስትወርድ ተከታትለው ሲጎትቷት እና ሱሪዋን ለመቅደድ ሲሞክሩ የምትታየው ታዳጊ ሴት እና የከበቧት ሰዎች
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በሲዳማ ክልል፣ ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን፣ በወንዶ ገነት ከተማ ሴቶች 'ቀሚስ እንጂ ሱሪ መልበስ የለባቸውም' በሚል በሴቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ መድረሱን ተከትሎ ጉዳዩ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህንን የተመለከቱ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርተዋል።

በወንዶ ገነት ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ እሸቱ ዳንኤል ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ሰብዓዊ መብት ስለጣሱ ክስ ይመሠረትባቸዋል" ብለዋል።

አቶ እሸቱ እንዳሉት፤ በከተማው ውስጥ ባለው የጫት ገበያ አካባቢ ትናንት መስከረም 20/ 2018 ዓ. ም. ወጣቶች "የተሳሳተ መረጃ መነሻ" በማድረግ የሴቶን "ሱሪ ለማውለቅ" በመመኮር ባደረሱት ፆታዊ ትንኮሳ "ቀንደኛ" ያሏቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ትናንት ከሰዓት 11 ሰዓት አካባቢ "ሱሪ የለበሰች ሴት ካገኛችሁ አውልቁ ተብለናል" በሚል ሴቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳው ደርሷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ላይም በታዳጊ ወንዶች የተከበቡ ሴቶች ሲሳደዱ እና ልብሳቸው በስለታማ ነገሮች ሲቀዳደድ ታይቷል።

"የጫት ገበያ 11 ሰዓት ስለሚደራ የጫት ገበያ ሙቀት በሚመስለ መልኩ ነው የተነሳው። ሰው ግር ብሎ ነበር" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ እሸቱ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የተዘዋወረውን ተንቀሳቃሽ ምሥል አስመልክተውም "ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀችውን ልጅ ማሳደድ ሲጀምሩ ሕዝቡ ተከላካይ ሆነ። ልጅቷን እያሳደዱ ሱሪ ለማውለቅ መሞከርና ሱሪ መቅደድ ነበር" ብለዋል።

"እስከ 6 የሚደርሱት ቀንደኛ ቀንደኛ የሚባሉት ታስረዋል። ምርቃና ብቻ ሳይሆን አደንዛዥ ነገርም ስለሚጠቀሙ በራሳቸው ፈጥረው የጀመሩት ወሬ ነው። ከማንም ያገኙት መረጃ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ሳምንት የአገር ሽማግሌዎች ተሰባስበው በአካባቢው የሚሰጠው የጥሎሽ ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደጨመረ ውይይት እንዳደረጉና "የጥሎሽ ዋጋ 15 ሺህ ብር ይሁን" የሚል ስምምነት ላይ እንደደረሱ ገልጸዋል።

በዚህ ውይይት ላይ "ስለ ሴቶች አለባበስ" ምንም የተነሳ ነገር ባይኖርም "ሱሪ የምትለብስ ሴት ሱሪዋ ተቀዶ ራቁቷን እንድትሄድ ትደረግ ተብሏል ብለው የጀመሩት እንጂ መነሻው አይታወቅም" በማለት አቶ እሸቱ አብራርተዋል።

አቶ አክሊሉ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ራቅ ካለ ገጠራማ አካባቢ ሱሪ መልበስ ለሴቶች ተገቢ አይደለም" የሚል ውይይት ተካሂዷል የሚል ወሬ ተናፍሷል ብለዋል።

"ይህን ብለው ተወያዩ መሰለኝ። እዚህ ዱርዬዎች እሱን ሰምተው ነው ወንዶ ገነት ከተማ ውስጥ ችግር የፈጠሩት። የከተማ ቦዘኔዎች ናቸው። የሚረቡ ልጆች አይደሉም" ሲሉም አክለዋል።

"በድንገት የተፈጠረ ነገር ነው። ብዙ ሰው የሰማውም ጉዳይ አይደለም። ነገሩን የተናገሩት የአገር ሽማግሌችም አይደሉም፤ የሃይማኖት አባቶችም አይደሉም" ያሉት አቶ አክሊሉ "ሕዝቡ ደርጊቱን ተቃውሞታል" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ እሸቱ ከነዋሪው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ትናንት ማምሻውን ሕዝቡ 'እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ይደረጋል' ብሎ ተቃውሞውን መግለጹን አክለዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ምን አሉ?

በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት የተጋራውን ተንቀሳቃሽ ምሥል እና ጽሑፍ ካዩ በኋላ ቁጣቸውን በተለያየ መልኩ ገልጸዋል።

ድርጊቱን በአንድ ድምጽ ያወገዙት የማኅበራዊ ሚደያ ተጠቃሚዎቹ የከተማው አስተዳደር እንዲሁም ክልሉ በፍጥነት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።

አካሉ በቀለ በሚል ስም የሚጠቀሙ ግለሰብ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ "ወንዶ ገነት እየሆነ ባለው አዝኛለሁ" ሲሉ በድርጊቱ የተሰማቸውን አስፍረዋል።

አክለውም ሕግ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

ወሰን ገብረ ኪዳን የተባሉ ደራሲ እና ጋዜጠኛ በበኩላቸው ". . .እህቶቹን የሚዋርድ "ወጣት" የዜጎችን ነፃነት ለመግፈፍ በዚህ ልክ መትጋቱ ያሳፍራል። . . . ሴቶችን በአደባባይ ሲዋርዱ የነበሩ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ይህ አስፀያፊ ድርጊት ወደሌላ ክልል ተዛምቶ የከፋ ችግር ከመከሰቱ በፊት በይፋ "ሃይ" ሊባል ይገባል" ሲሉ ሐሳባቸውን በፌስቡክ ልጥፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ምናሴ ዋቆ ጉደታ የሚባሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው "የክልሉ መንግሥት ይሄን አስነዋሪ የወንጀል ድርጊት አስቁሞ ወንጀለኞቹን በሕግ ይጠይቅልን። የተፈጠረውንም ነገር በጥንቃቄ መርምሮ በግልፅ ያስረዳን" ሲሉ ረዘም ያለ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው እያስፔድ ተስፋዬ በበኩሉ ". . . እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ ግብረገብ (Moral) እና ግብረገባዊ ፋይዳ (moral value) መመንጨት እና መተግበር ያለበት ከባህል... ከሽምግልና... ከሃይማኖት ወዘተ ሳይሆን ከመንግሥት ሊሆን እንደሚገባው ከዚህ በላይ ማሳያ የለም" ሲል ሐሳቡን በፌስቡክ ገፁ ላይ አጋርቷል።

ጦማሪ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ሀይሉ በበኩሉ የወንዶ ገነት አስተዳደር በፌስቡክ ገፁ ላይ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መግለፁን ተከትሎ "የወንዶ ገነት መስተዳድር ድርጊቱን አውግዞ፣ተሳታፊዎቹን ለፍርድ እንደሚያቀርብ አሳውቋል። ውሳኔው ከፍፃሜ እንደሚደርስ ተስፋ እያደረግኩ፣ለእርምጃው ምስጋናዬን እገልጻለሁ" ብሏል።

የወንዶ ገነት ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እሸቱ በበኩላቸው የአገር ሽማግሌዎች ውይይት ከአለባበስ ጋር እንደማይገናኝና ስለ ጥሎሽ ያደረጉትንም ንግግር ለሕዝብ ይፋ እንዳላደረጉ ገልጸዋል።

"ከባህል ወይም ከሽማግሌዎች ንግግር ጋር የተያያዘ ሳይሆን ልጆቹ ዝም ብለው ሱሪ አውልቁ ብለው ነው የጀመሩት። ሽማግሌዎችም አልተወያዩም። ሱሪ ልበሱም አትልበሱም አልተባም። ሱሪ መልበስ ሰብዓዊ መብት ነው።"

አያይዘውም "ወሬው ምንጩ አይታወቅም። ውይይትም አልተደረገም። ሽማግሌዎች ባለፈው ሳምንት ስለ ጥሎሽ መብዛት ነው የተወያዩት። እሱም በይፋ አልታወጀም። ወደ ሕዝብ አውጥተው አላወጁም ተግባራዊም አልተደረገም" ብለዋል።

አቶ እሸቱ "ወሬ የሚያናፍሱ፣ችግር መፍጠር የሚፈልጉ ዱርዬዎች ሱሪ የምትለብስ ሴት ሱሪዋ ተቀዶ ራቁቷን እንድትሄድ ትደረግ ተብሏል ብለው የጀመሩት እንጂ መነሻው አይታወቅም" በማለትም አክለዋል።

ቢቢሲ፤ ከወንዶ ገነት ከተማ ከንቲባ እንዲሁም ከሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ቢደወልም አልተሳካም።