'ፎቶው የእሱ ነው' የሚል ማስረጃ እስከማጻፍ የደረሰው የከንፈር መሰንጠቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“በደንብ የማስታውሰው ልጅ አለ። በቅርቡ ነው ቀዶ ህክምና የተሠራለት። ህክምናው ስኬታማ ነበር። ቀጥሎ ‘ዶ/ር ማስረጃ ይጻፉልኝ’ አለ። ‘ለምን? ምን ያደርግልሃል?’ አልኩት። ‘በቅርቡ ፈተና እፈተናለሁ። የተነሳሁት ፎቶ ከአሁኑ ፊቴ ጋር ስለማይመሳሰል አትፈተንም እንዳልባል ነው’ አለኝ” ይህንን ገጠመኛቸውን ሊቢቢሲ ያጫወቱት ዶ/ር አብርሃም ናቸው። 

ዶ/ር አብርሃም ገ/እግዚአብሔር የፕላስቲክና ሪኮንስትራክሽን ቀዶ ህክምና ባለሙያ ናቸው።

ይህ ከከንፈር እና ከላንቃ መሰንጠቅ ጋር በተያያዘ ከሚያስታውሷቸው በርካታ ታሪኮች አንዱ ነው። 

ኤዶምን የሚያውቅ ሁሉ ሳቂታ እና ተጫዋች በሚል ነው የሚገልጻት። (ትክክለኛ ስሟ እንዳይገለጽ ስለጠየቀች ኤዶም እያልን እንቀጥላለን።)

ዕድሜዋ በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኛል። 

ኤዶም በአንድ ጉዳይ የልጅነት ጊዜዋን በበጎ አታስታውስም።

ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንደ አሸን ተስፋፍቷል። 

ጓደኞቿ የልጅነት ፎቷቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲለጥፉ እሷ ግን “በጭራሽ የማላደርገው ነገር ነው ትላለች።"

እኩዮቿ በተለይ ልደታቸውን ሲያከብሩ ‘የቀድሞ እና የአሁኑ’ እያሉ የልጅነት ፎቷቸውን ሲለጥፉ ታያለች።

ይህንን ነው “በጭራሽ የማላደርገው" የምትለው።

ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የምታደርገው የከንፈሯ መሰንጠቅ ያደረሰባትን ተጽዕኖ ነው።

ኤዶም ስትወለድ ከንፈሯ ተሰንጥቆ ነው።

“ልጅ ሆኜ ብዙ ሰዎች ያፈጡብኝ ነበር።” ትላለች።

ብዙውን ነገርም አታስታውስም። እናቷ ናቸው የሚነግሯት።

ኤዶም ያደገችው አራት ልጆች ያሉት ቤተሰብ ውስጥ ነው።

እንደተወለደች ነርሷ አንድ ነገር እንደተፈጠረ ስታጉተመትም እናቷ ሰምተዋል።

ግራ የተጋባውን ፊቷን አይተው ‘ምን ሆና ይሆን ልጄ?’ የሚለው ነገር በአዕምሯቸው ተመላልሷል።

“[እናቴ ከከንፈር መሰንጠቅ ጋር] በመወለዴ ደንግጣ ነበር። አንዳንዴም ‘ምን አጥፍቼ ይሆን?’ የሚል ጥያቄም ነበራት” ትላለች።

የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማት እንደነበርም አጫውተዋታል።

‘ምን አጥፍቼ ይሆን?’ ከሚለው በተጨማሪ የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ ነበር ከባድ የሆነባቸው።

የትም ሲሄዱ በነጠላ ሸፋፍነዋት ነበር። 

ኤዶም ሦስት ዓመት ሲሆናት ወደ ህክምና አቀናች።

ቀላል ነበር ችግሯ። የከንፈር መሰንጠቅ ብቻ ነው።

የከንፈር መሰንጠቅ በተለያየ የዕድሜ ክልል ይከሰታል።

የከንፈር መሰንጠቅ በተፈጥሮ ወይንም በሌላ ምክንያት የላይኛው ከንፈር ሳይገጥም ሲቀር ወይም ለሁለት ሲከፈል የሚከሰት ነው። 

አንዳንድ ጊዜ መሰንጠቁ ሁለት ቦታ ጭምር ሊሆን ይችላል። 

አንዳንዴም ከከንፈር አልፎ እስከ ላንቃ መሰንጠቅ ይደርሳል።

ኤዶም ከከንፈር መሰንጠቅ ጋር ብቻ ነው የተወለደችው።

“በምን ምክንያት ችግሩ እንደተከሰተብኝ አላውቅም። ቤተሰባችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም” ትላለች።

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ በብዙ ምክንያቶች ሊያጋጥም እንደሚችል ዶ/ር አብርሃም ይናገራሉ።

የህክምና ባለሙያው ችግሩ በኢንፌክሽን ምክንያት ሊከሰት እንዲሁም በተፈጥሮ ወይንም በሌሎች ምክንያቶች ሊፈጠር እንደሚችል ያስረዳሉ።

“የከንፈር መሰንጠቅ በሁለት ሦስት መንገድ ሊመጣ ይችላል። በብዛት የሚመጣው ግን በተፈጥሮ ነው” ይላሉ ዶ/ር አብርሃም። 

ችግሩ ቤተሰብ ውስጥ ካለ አዲስ በሚወለድ ልጅ ላይ የመከሰት ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው።

ሌላው ምክንያት ደግሞ በእርግዝና ወራት የሚወሰድ መድኃኒት ነው።

በእርግዝና ወቅት ለቫይረስ ወይም ለአደገኛ ኬሚካል መጋለጥም ለከንፈርና ለላንቃ መሰንጠቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በአንድ ምክንያት ብቻ ወይንም የተለያዩ መንስዔዎች ተደራርበው የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅን እንደሚያስከትሉ ዶ/ር አብርሃም ይናገራሉ።

“ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በብዛት የሚከሰተው በተፈጥሮ ነው” ይላሉ ዶ/ር አብርሃም።

ቤተሰብ ውስጥ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ካለ አዲስ የሚወለዱ የቤተሰብ አባላት ከችግሩ ጋር የመወለድ ዕድላቸው ከፍ ይላል።

ለምሳሌ ቤት ውስጥ አባት፣ እናት ወይንም እህት እና ወንድም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ካለባቸው አዲስ የሚወለድ የቤተሰቡ አባልም ከዚህ ችግር ጋር የመወለዳቸው ዕድል ይጨምራል።

በእርግዝና ወቅት አልኮል እና አደንዛዥ ዕጽ መውሰድም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ የማስከተል ዕድል አላቸው።

“በተለይም በእርግዝና የመጀመሪያ ሦስት ወራት በሚወሰድ መድኃኒት ሊከሰት ይችላል። በእርግዝና ወቅት ፎሊክ አሲድ እና ቫይታሚን ያላገኙ እናቶች የከንፈር መሰንጠቅ ያለባቸው ልጆችን የመውለድ ዕድላቸውም ከፍ ይላል” ይላሉ።

ከዚህም ባሻገር ያልተመጣጠነ ምግብ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የመከሰት ዕድሉ ይጨምራል።

ከሥርጭት አንጻር ከታየ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ከጥቁሮች ይልቅ ነጮች ላይ በስፋት ይታያል።

ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን በሁለት እጥፍ እንደሚያጠቃም መረጃዎች ያሳያሉ።

ስለዚህ ኤዶም የከንፈር መሰንጠቅ ያጋጠማት ከእነዚህ መካከል በአንዱ ሊሆን ይችላል።

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ምን ዓይነት ተፅዕኖዎች ያደርሳል?

ኤዶም ችግሩ መኖሩ ያስከተለባትን ችግር ብዙም አታስታውሰውም።

“ብቻ ፎቶዬን ስመለከተው ደስተኛ አይደለሁም። ከዛ ውጭ ያደረሰብኝን ነገር አላውቀውም” ትላለች።

 ዶ/ር አብርሃም ግን የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ እንደ ጉዳቱ መጠን ችግሩም የተለያየ መሆኑን ይገልጻሉ።

 “የላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ካለ ምግብ በሚበላበት ወቅት ምግብ ወደ አፍንጫ ይገባል።ይህም ትንታ ይፈጥራል። ደረቅ እና ለስላሳ ላንቃ አለ። ለስላሳው ላንቃ ወደ ኋላ ያለው ነው። ይህ በመዘጋት እና በመከፈት አየር ወደ አፍንጫ እንዲገባ እና እንዲዘጋ ያደርጋል። በምንበላበት ጊዜ ምግብ ወደ አፍንጫ እንዳይሄድ [ለስላሳዋ ላንቃ] ትዘጋለች፤ ስንተነፍስ ግን ትከፈታለች። ስትሰነጠቅ ይህንን ማድረግ ታቆማለች” ይላሉ።

ችግሩ በንግግር ላይም ተፅእኖ ያሳድራል።

በአፍንጫ እና በላንቃ የሚፈጠሩ ድምጾች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን ድምጾች እንዲፈጠሩ ከንፈር ያለው ሚና ሲታሰብ ደግሞ የችግሩን ጥልቀት መገመት ይቻላል።

“አንዳንዴም የተወሰኑ ድምጾችን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ እንዲለመዱ ያደርጋል” ይላሉ።

ችግሩ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም።

“አንዳንድ ጊዜ ጥርስ እና ድድ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። ኢንፌክሽንም ሊፈጥር ይችላል” ይላሉ ዶ/ር አብርሃም።

የጆሮ ህመምም ከከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ የሚከሰትበት ዕድል አለ። 

ይህ የጆሮ ኢንፌክሽን ዘላቂ የመስማት ችሎታን እስከማጣት ይደርሳል።ገጽታም ስለሚበላሽ ተጽዕኖው ሰፊ የሚባል ነው። 

ይህ ተጽዕኖ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን ከኋላው ያስከትላል።

ለዚህም ነው ኤዶም የልጅነት ፎቶዎቿን ለማሳየት የምትሳቀቀው። 

የከንፈርና የላንቃን መሰንጠቅ በሰውነት ቅርጽ ላይ ለውጥ ስለሚያመጣ በቀላሉ በምርመራ ማወቅ ይቻላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምን አይነት ህክምና ይሰጣል?

በእርግዝና ወቅት ልጅ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ እንዳለበት በአልትራሳውንድ ምርመራ ማወቅ ይቻላል።

በጊዜ መታወቁ ወላጆች በሥነ ልቦና ተዘጋጅተው በፍጥነት ወደ ህክምና እንዲያመሩ ይረዳል።

ይህ ካልሆነ ግን ሕጻኑ እንደተወለደ አካላዊ ምርመራ ተደርጎለት የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ እንዳለበትና እንደሌለበት ማወቅ ይቻላል።

ከተከሰተ ደግሞ ህክምና አለው። 

እንደ ዶ/ር አብርሃም ከሆነ “እንደ ችግሩ ስፋት በተለያየ ደረጃ የሚሰጥ ተከታታይ የሆነ ህክምና ነው ያለው።” 

በተፈጥሮ የተከሰተ ከሆነ በፍጥነት የቀዶ ህክምና ማከናወን ይመከራል።

“ልጆች ቋንቋ ሳይጀምሩ ከስድስት ወር በፊት ህክምና ቢደረግ ይመረጣል። ካልሆነ አነጋገር ላይ መሰረታዊ ችግር እንደተፈጠረ ይቆያል። የላንቃ መሰንጠቅ ካለም ከ18 ወራት በፊት ህክምናው መከናወን አለበት” ይላሉ።  

ችግሩ በአፍንጫ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰም ተጨማሪ ቀዶ ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ ቀዶ ህምናው እስኪሰራለት ድረስ የሕጻኑን ላንቃ በሰው ሰራሽ ፕላስቲክ በመዝጋት እንዲመገብ ማድረግ ይቻላል።

ጥርስ እና ድድም ጉዳት ሊኖረው ይችላል። 

በዚህ ወቅት ለንግግርና ለጥርስ ህክምና ተደጋጋሚ ክትትል ያስፈልጋል። 

ከዚህም ሌላ ጥርሶች ጉዳት ከደረሰባቸው ለማስተካከል ቀዶ ህክምና ይሰጣል።

የጆሮ ህክምናም እንዳስፈላጊነቱ በቀጣይነት ይሰጣል።

በዚህ ምክንያት ተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። 

ይህንንም ነው ዶ/ር አብርሃም 'በፓኬጅ ' የሚሰጥ ህክምና የሚሉት።

ተከታታይ የሆነ ሁሉንም ችግሮች ለመቅረፍ የሚከናወን ህክምና እንደማለት ነው።

ትልቁ ነገር ደግሞ የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት ነው። 

ይህ ደግሞ ለታካሚዎች እና ለቤተሰቦች የሚሰጥ ነው።

ከዚህ ሁሉ ህክምና በኋላ ደግሞ በመጨረሻም የቤተሰብ ድጋፍ  እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አብርሃም አፅንኦት ይሰጣሉ።

ህክምናው በተለያዩ ተቋማት የሚሰጥ ሲሆን እንደ ችግሩ ስፋት በአንድ ቦታ ሊሰጥ፣ አንዳንዴም በተለያዩ ቦታዎች የሚሰጥበት አጋጣሚ እንዳለ ባለሙያው ያስረዳሉ።

በተለያዩ የህክምና ተቋማትም በዘመቻ መልክ በነጻ ህክምናው ይሰጣል። 

በቅርቡ የአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 20 ሚሊዮን የወጣበት የህፃናት የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ የቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል አስመርቋል።

በተለይም የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ህጻናት ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ነው ተብሏል።

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ወራት በጽንሱ ላይ የሚከሰት ነው።

ችግሩ በተፈጥሮ የሚመጣ ከሆነ መከላከል አይቻልም።

ከአካባቢያዊ ተጽዕኖ የሚመጣ ከሆነ በእርግዝና ወራት ለዚህ ጉዳት መነሻ የሆኑ ነገሮች ላይ በሚደረግ ጥንቃቄ መከላከል ይቻላል።

ስለዚህ ከእርግዝና በፊት የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅምን በማረጋገጥ፥ የተመጣጠነ ምግብን በመመገብና ቫይታሚን በመውሰድ መከላከል ይቻላል።

በእርግዝና ወቅት ያለጤና ባለሙያ ምክር ምንም አይነት መድኃኒት ባለመውሰድ፣ ባለማጨስ፣ አልኮል ባለመጠጣት እና ከጨረር የሚያጋልጡ ነገሮች ራስን መጠበቅም አስፈላጊ ነው።

ከተከሰተም በፍጥነት ወደ ጤና ማዕከላት ማቅናት ይመከራል። 

ዶ/ር አብርሃም ፊቴ ስለተቀየረ ማስረጃ ይስጡን ካሏቸው ታካሚያቸው በተጨማሪ ሌላ የሚያስታውሱት ገጠመኝም አላቸው።

“ይህ ጓደኛዬን የገጠመው ነው" ሲሉ ይጀምራሉ።

 "እናት የልጇ ቀዶ ህክምናው ከተጠናቀቀ በኋላ እያለቀሰች ‘ልጄን ሰው ፊት አላቀርባትም ነበር። በተደጋጋሚ ልገላት ሳሰብ ቆይቻለሁ። እንዴት እንደምገላት ሳስብ ነበር። ልጄን በድያታለሁ” እያለች ስቅስቅ ብላ አለቀሰች” ሲሉ አጫውተውናል።

ኤዶም አሁንም ከንፈሯ ላይ ጠባሳ አለ።

ጠባሳው ግን በጣም ትንሽ ነው። 

“አንዳንዶች ‘ወድቀሽ ነው?’ ይሉኛል ጠባሳውን እያዩ [ሳቅ]” ትላለች

ኤዶም ተጫዋች እና ሳቂታ ናት። 

የምትስቂው ያለፈውን ህመምሽን ልትበቀይው ነው? ተብላ ስትጠየቅ “ይሆናል" ስትል በሳቅ የታጀበ መልስ ሰጥታለች።